የአውሮፓ እና አሜሪካ መኪና አምራች ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ቻይና በማዞር ላይ እንደሆኑ ተገልጿል
ቻይና የዓለምን የመኪና ሽያጭ በመቆጣጠር ላይ መሆኗ ተገለጸ
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለዓለም ገበያዎች በማቅረብ ቀዳሚ መሆኗ ተገልጿል፡፡
እንደ ሲኤንኤን ቢዝነስ ዘገባ ተሸከርካሪዎችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ቀዳሚ የነበረችው ጃፓን በቻይና ተቀድማለች፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ 50 የቻይና ኩባንያዎች 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ሸጠዋል ተብሏል፡፡
ቢዋይዲ፣ ቴስላ ቻይና፣ ኤክስፔንግ ብዙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ውጭ ሀገራት የላኩ ኩባንያዎች ሲሆኑ አውሮፓ እና የአሜሪካ ሀገራት ደግሞ ዋነኛ የገበያ መዳረሻዎች ነበሩ፡፡
የቻይና ተሽከርካሪዎች በዋጋ፣ በጥራት እና በአገልግሎት ጊዜ በአውሮፓውያን ሸማቾች ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸው የጀርመን፣ ፈረንሳይ ብሪታንያ ስሪት የሆኑ ተሸከርካሪዎችን እየተፎካከሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የፈረንሳዩ ሪናልት የተሸከርካሪ አምራች ኩባያ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሉካ ደ ሚኦ እንዳሉት የቻይና ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባያዎችን አልቻልናቸውም ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከ2035 ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን እንደሚያግድ መግለጹ የአውሮፓ ኩባያዎችን ጎድቷል የሚሉት ስራ አስኪያጁ በቻይና የሚመረቱ ተሽከርካሪዎች ተመራጭ ሆነዋልም ብሏል፡፡
ቻይና የኤሌክትሪክ ባትሪዎችን ለመስራት የሚያገለግለው ሊቲየም ማዕድን ዋና ሻጭ ሀገር ነች የተባለ ሲሆን 60 በመቶ የዓለማችን ሊቲየም አቅራቢ ሀገር ናት፡፡
የቻይና ኩባንያዎች ወደ ዘጠኝ የአውሮፓ ሀገራት ከ350 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የላኩ ሲሆን በአምስት ዓመት ውስጥ የአውሮፓ የገበያ ድርሻቸውን ወደ 300 በመቶ የማድረስ እቅድ መያዛቸው ተገልጿል፡፡
የአውሮፓ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች ቤጂንግን ለመፎካከር የማምረቻ ቦታዎቻቸውን ወደ ቻይና በማዞር ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን ርካሽ የሰው ሀይል እና የሊቲየም ማዕድን ፍለጋ ለኩባንየዎቹ መሰደድ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ የቻይናን ግስጋሴ ለመከላከል የተለያዩ መሰናክሎችን እየፈጠሩ ቢሆንም የቻይና ኩባንያዎች ግን በተለያዩ መንገዶች መፎካከራቸውን ቀጥለዋል ተብሏል፡፡