በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ስላሉ ግድያዎች ገለልተኛ ኮሚሽን ተቋቋሞ ምርመራ እንዲያደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ
አመራር ሆነው የመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና በጥቃቱ የተሳተፉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል
ጥቃቶችን ለማስቆም በመንግስት የሚደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ 5 ፓርቲዎች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል
በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም በጥልቀት መርምሮ ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ(ባልደራስ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ እናት ፓርቲና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ፣ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለውን ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ በተመለከተ ትናንት መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የግድያዎች መስፋፋትና መደጋገም በሀገር አንድነትና ደህንነት ላይ የደቀነው ከፍተኛ አደጋ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትና ዘላቂ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
እስካሁን በኢትዮጵያ በተፈፀሙት ጥቃቶች ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዲወሰድም ፓርተሪዎቹ በመግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አመራሮች ሆነው የመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና በጥቃቱ የተሳተፉትን መንግስት አጣርቶ በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርም ፓርቲዎቹ በጋራ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን፣ በአማራ ሕዝብ ላይ “በጥላቻ ኃይሎች እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት ለማውገዝ፣ ለማጋለጥና ለፍርድ ለማቅረብ” ያለምንም ልዩነት በጋራ እንዲሰለፉም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ “የጥፋት ፖለቲካ ተዋንያን የሆኑ ጽንፈኛ ስብስቦች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያራምዱትን የጥላቻ ትርክት” ተከትለው የሚፈጸሙ ተከታታይ ዘር ተኮር ጥቃቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህን ጥቃቶች ለማስቆም የሚደረገው መንግስታዊና ሀገራዊ ጥረት “ፍጹም የማይመጥንና በቂ እንዳልሆነ እንገነዘባለን” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡ በተለይ እየተፈጸሙ ያሉት ጥቃቶች በርካታና ተደጋጋሚ መሆናቸው፣ በመንግስት በኩል ከሚታየው “ለከት የለሽ ዳተኝነት” በተጨማሪ “በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ጭምር በጥቃቶቹ መሳተፋቸው” ስጋቱንና አደጋውን ውስብስብ እንዳደረገው ፓርቲዎቹ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እና በአጠቃላይ “መጤ” ተብለው በተፈረጁ ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት እንደሚያወግዙም ገልጸዋል፡፡