የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ በተፈጸመው ጥቃት 28 ሰዎች መሞታቸውን አስታወቀ
በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል 16 ወንዶችና 12 ሴቶች መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል
“ኦነግ ሸኔ የሁሉም ጠላት ነው”- የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ በተፈጸመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 28 መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አስታወቁ፡፡
ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፣ በዞኑ ቦኔ ቀበሌ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው በዚህም 28 ንጹሃን መገደላቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ግድያው የተፈጸመው 3 ሰአት አካባቢ ዜጎቹን ከቤታቸው በግድ በማስወጣት በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ጥቃት ስለመፈጸሙም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በጥቃቱም በግድ ካስወጣቸው 50 ሰዎች መካከል 28 ሲገደሉ፤ 12 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።
በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል 16 ወንዶችና 12 ሴቶች መሆናቸውም ነው የገለጹት ኮሚሽነሩ “ተስፋ የቆረጠው ኦነግ ሸኔ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሟል፤ ይህም የቡድኑን የለየለት ሽብርተኛ መሆኑን አሳይቷል ነው “ ሲሉ ተናግረዋል።
ጥቃቱ የኦሮሞም የአማራም ተወላጆች ላይ መፈጸሙን ያስታወቁት ኮሚሽነር አራርሳ፤ ሁኔታው ከተከሰተ በኋላ ለማረጋጋት በስፍራው የደረሰው ሃይል በወሰደው ርምጃ ሶስት ሰዎች ከነትጥቃቸው መደምሰሳቸውን ገልጸዋል።
አጥፊ ቡድኑ 80 በመቶ ጉዳት ሲያደርስ የነበረው የኦሮሞ ብሔር ላይ እንደሆነም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ቡድኑ የሕዝብ ቅራኔ ለመፍጠር ሲባል የአማራ እና ሌሎች ብሔረሰቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃት ማድረሱን ቀጥሏል ያሉት ኮሚሽነር አራርሳ ፓሊስ አልደረሰልንም የሚለው ግን ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል።
“ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ርምጃ አልተወሰደም እየተባለ የሚናፈሰው ሃሰት ነው፤ ከዚህም ቀደም በመሰል ሁኔታዎች የተፈጠረውን ስናጣራ ሃሰት ሆነው አግኝተናቸዋል፣ በቀጣይ ማጣራት ትዕዛዝ ደርሶት ያልፈፀመ ሃይል ካለ ግን ይጠየቃል” ብለዋል።
“ኦነግ ሸኔ የሁሉም ጠላት ነው” ያሉት ኮሚሽነር አራርሳ፣ ከዚህ ቀደም በተወሰደ ርምጃ ከ2ሺ 600 በላይ ሃይሉን ማጣቱን ተናግረዋል።