በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ
በዘለቄታዊ መፍትሄው ላይ እንደ አማራ ለመምከር በቅርቡ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሕዝብ መድረክ እንደሚዘጋጅም ገልጿል
ፓርቲው ትላንት ምሽት በወረዳው በአማራው ላይ የቡድን ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ
“በትናንትናው ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዘርን መሠረት ያደረገ የአማራን የቡድን ጥቃት አረጋግጠናል” ሲል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ መግለጫ አውጥቷል።
የጥቃቱን መጠንና ዝርዝር ሁኔታዎች ከፌዴራሉና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እያጣራን ነው ያለው ፓርቲው በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት የአማራ ህዝብና ድርጅታችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክፉኛ አዝኗል፤ ተቆጥቷል ብሏል፡፡
በመሆኑም ይህ ድርጊት የሚወገዝ ከመሆኑም በላይ አጥፊዎቹ እንደየስራቸው በህግ አግባብ ሊዳኙ ይገባልም ብሏል ፓርቲው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አካለት ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲል ማሳሰቢያ አውጥቷል፡፡ ማሳሰቢያው የሚከተለው ነው፡-
1) የፌደራሉ መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ በየ አካባው እየደረሰ ያለውን ተደጋገሚ ዘር ለይቶ የማጥቃት ወንጀል ዋነኛ የብሔራዊ ደኀንነት አደጋ አድርጎ ሊወስደው ይገባል። ስለሆነም የኢፌዴሪ ብሔራዊ የደኀንነት ምክር ቤት የአደጋውን መጠንና ቀጠናዊ መዘዝ በማጤን ዘርን መሠረት ያደረገው የአማራ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ ስለ ጥቃቱም ዝርዝር መረጃ ለመላ ኢትዮጵያዊያን እንዲሰጥ፤ በአማራው ጥቃት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ የጥፋት ኃይሎች ላይ ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እንጠይቃለን፤
2) የአማራ ህዝብ የሚኖርባችው ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት፣ እናንተንና የአካባቢውን ወንድም ህዝብ አምነው አገር አለን ብለው፤ ሕግና ሥርዓት አለ በሚል ኢትዮጵያዊ መተማመን ከናንተው ጋር ለዘመናት የኖሩትን የአማራ ተወላጆች ከመቸውም ጊዜ በላይ ጥበቃ እንድታደርጉላቸውና ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤
3) በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ተከታታይ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ፤ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ አማራን በየ አቅጣጫው በመውጋት በንጹሃን ደም የፖለቲካ ቁማር የሚሰራው “የመቀሌው ግዞተኛ የትህነግ ቡድን” በመሆኑ፣ “ይህ ኃይል “የብሔራዊ ደኀንነታችን የስጋት ምንጭ ከመሆን አልፎ የሽብርና የቀውስ ማዕከል” ስለሆነ ለኢትዮጵያና ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም ሲባል ከመለሳለስና ከመሸከም ፖለቲካ ወጥቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስርአት እንዲይዝ ለማድረግ ጊዜው አሁን ስለመሆኑ እናስረግጣለን፤
4) የኢትዮጵያ ዘብ የመሆን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ያለባችሁ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አካላት የአማራ ህዝብና ሌሎች ብሔሮች በማንነታቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ስትከፍሉት የቆያችሁትን መስዋዕትነት መቼም አንዘነጋውም። ዛሬም ከሀገራዊ ለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ጸረ-ሕዝብ የሆኑ ኃይሎች አማራውን ዘሩን መሰረት አድርገው ጥቃት እየተፈጸሙበት መሆኑን አውቃችሁ፤ በየአካበቢው ለሚኖረው አማራ ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ በመስጠት፤ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኳችሁን እንድትወጡ በድጋሚ እናሳስባለን፤
5) የአማራ ህዝብ፣ ምሁራን፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፦ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የረዥም ጊዜ የተዛባ ትርክት ውጤት መሆኑን በመገንዘብ፤ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት፣ ለሦስት አስርታት የገጠመንን መዋቅራዊ ማነቆ ለመቅረፍ በሚመጥን ልክ የመፍትሄ ሃሳብ በማመንጨት የበኩላችሁን እንድትወጡና በጋራ በመቆም የአማራ ህዝብ ከተደቀነበት የህልውና ስጋት እንድታደገው 'የአማራ አንገቱ አንድ ነው' በሚል ወገናዊ ጥሪያችን እናቅርብላችኋለን፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በዘለቄታዊ መፍትሄው ላይ እንደ አማራ ለመምከር በቅርቡ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሕዝብ መድረክ እንደሚዘጋጅም ፓርቲው ገልጿል፡፡
ትናንት ምሽት በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀናቲ ቀበሌ ኦነግ ሸኔ በፈፀመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን በጭካኔ ህይወታቸውን ማጥፋቱን የኦሮሚያ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዛሬ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡