“እንደ አማራ ክልል አስቸኳይ ምክክርም ንግግርም እንፈልጋለን”- አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ በርካታ ንጹሃን በማንነታቸው ተለይተው መገደላቸው የሚታወስ ነው
“የቤኒሻንጉል ጉምዝ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታት እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት በገዳዮች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ”ም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል
የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር “በአማራ ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ለማስቆም” የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ “አስቸኳይ ውይይት” እንደሚፈልግም አስታወቁ።
ርእስ መሥተዳድሩ “ባለፉት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ በተሠራው የጥላቻ ትርክት አማራ በሚኖርበት አካባቢ መገደል፣ መሳደድና መፈናቀል እየደረሰበት ነው፤ ይህ ጉዳይ እንዲቆም ከፌደራል እና ከክልል መንግሥታት ጋር በጋራ እየሠራን ነው” ብለዋል።
የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
አቶ አገኘሁ በሰሞነኛ የአማራ ብሔር ተወላጆች ግድያ ጋር በተያያዘ ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው “በተለይም ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን አማራን ነጥሎ በማጥቃት የሚታወቅ ነው” ያሉት አቶ አገኘሁ “የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነፃ አውጭ ነኝ የሚል ቡድንም በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሰ ነው” ብለዋል እንደ አብመድ ዘገባ።
በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት።
በሰሞነኛው ግድያ የክልሉ መንግሥት ማዘኑንም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ጉዳዩ የሃገሪቱን ዜጎች ተቻችሎ መኖር ለችግር የሚያዳርግ ነው ያሉም ሲሆን የሁኔታው አለመሻሻል የክልሉ መንግሥት እንዳሳሰበው ተናግረዋል።
“የፌዴራል መንግሥት የጀመረውን የጸጥታ ማስከበር ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ ገዳዮቻችን የሚታወቁ ናቸው፤ በእነዚህ ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት” ሲሉም አስቀምጠዋል።
“የቤኒሻንጉል ጉምዝ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታት እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት በገዳዮች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ”ም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።
ለዚህም አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነንም ብለዋል።
አቶ አገኘሁ “በሀገረ መንግሥት ግንባታ የፖለቲካ ልዩነት ሊኖር ይችላል ህፃናትና እናቶች ግን መሞት የለባቸውም ነው” ያሉት።
“የሀዘን መግለጫ ማውጣት ሰልችቶናል፣ በጉዳዩ ላይ እልባት እንዲሰጥ እንፈልጋለን፤ እንደ አማራ ክልል መንግሥት አስቸኳይ ምክክርም ንግግርም እንፈልጋለን”ም ብለዋል።
ጉዳዩ እንዲቆምም አሳስበዋል።
ማንነታቸው ተለይቶ በአማራነታቸው ብቻ ለሚገደሉ ዜጎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል።
“ይህን ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቅመው የሀገራችን አንድነት ለመበታተን የሚጥሩ ኃይሎች ያስቡታል እንጂ አይሳካላቸውም፤ ይህ ጊዜ ያልፋልም ነው” አቶ አገኘሁ ያሉት።
ኦነግ ሸኔ ከኦሮሚያ አልፎ ወደ አማራ ክልል መግባቱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ “አንዳንዶች ኦነግ ሸኔ ስለመኖሩና ስላለመኖሩ ሊነግሩን ይፈልጋሉ፤ ምን አይነት መግለጫ ማውጣት እንዳለብን ሊነግሩን የሚፈልጉ አሉ ይህ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
የታቀዱ ሃገራዊ ግቦች እንዲሳኩ ግድያው መቆም አለበትም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሉት፡፡
ከትናንት በስቲያ ምሽት ሌሊቱን ጭምር በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ በርካታ አማራዎች በማንነታቸው ተለይተው መገደላቸውን አል ዐይን አማርኛ የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በጥቃቱ 28 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል ምንም እንኳን ቁጥሩ ከአንድ መቶ ሊያሻቅብ እንደሚችል ቢነገርም፡፡