ተጠባቂው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 50 ቀናት ብቻ ቀርተውታል
በምርጫው ላይ ለ5ኛ ጊዜ እጩ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ ዋነኛ ተፎካካሪ ናቸው
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ነሀሴ መጀመሪያ ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል
ተጠባቂው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 50 ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡
ኬንያን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመምራት እጩ ፕሬዝዳንቶች በምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ሲሆኑ አሁን ላይ ፉክክሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት አራት እጩዎች ቀርበው በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ካሉት እጩ ፕሬዝዳንቶች መካከል ባለፉት ምርጫዎች ላይ ለአራት ጊዜ ተወዳድረው ሽንፈትን ያስተናገዱት የኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንቱ ራይላ ኦዲንጋ ዋነኛው ተፎካካሪ ናቸው፡፡
ራይላ ኦዲንጋ በፈረንጆቹ 1997 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራቸውን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እጩ የነበሩ ሲሆን በምርጫው ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
በነዳጅ እና ሀይል ልማት ዘርፍ ነጋዴ የሖኑት የ77 ዓመቱ ኦዲንጋ ላለፉት አራት ተከታታይ ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ወቅቶች ላይ እጩ ቢሆኑም አብላጫ የህዝብ ድምጽ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
ውጤታቸውን ተከትሎም ራይላ ኦዲንጋ ከፕሬዝዳናታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ከአምስት ዓመት በፊት ቢናገሩም ዘግይተው በሰጡት መግለጫ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት መልሰው እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል፡፡
ኬንያን አሁን ላይ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገሉ ያሉት የዲሞክራቲክ ዩኒየኑ ዊሊያም ሩቶ ሌላኛው ዋነኛ ተፎካካሪ ናቸው፡፡
የ55 ዓመቱ ሩቶ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በግጭት ውስጥ ሲሆኑ የጸባቸው መንስኤ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ለራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ከራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ በተጨማሪ ኬንያን በፕሬዝዳንትነት እየተፎካከሩት ያሉት ቀሪዎቹ እጩዎች ዳቪድ ዌሂጋ ጆርጅ ዋጃኮያህ ናቸው፡፡
ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት 55 እጩዎች ቀርበው የነበሩ ቢሆንም በመጨረሻም አራት ብቻ ቀርተዋል፡፡
ኬንያን ላለፉት 10 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ኡሁሮ ኬንያታ የስልጣን ጊዜያቸውን ከሁለት ጊዜ በላይ ማራዘም ስለማይችሉ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት እንዲያስረክቡ የሀገሪቱ ህገ መንግስት ያስገድዳቸዋል፡፡