ሶማሊያ ከ2 አመት በፊት በኬንያ ጫት ላይ ጥላው የነበረውን እግድ ልታነሳ ነው
እርምጃው ኬንያታ በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሹመት ስነስርዓት ላይ ከተገኙ በኋላ የመጣ ነው
ኬንያ እና ሶማሊያ ለረዥም ጊዜ በዘለቀው የድንበር ውዝግብ ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ሻክሮ የቆየ ሀገራት ናቸው
ላለፉት ሁለት አመታት በኬንያ ጫት ላይ እገዳ ጥላ የነበረችው ሶማሊያ እገዳውን ልታነሳ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ሶማሊያ እገዳውን የምታነሳው ሁለቱም ሀገራት የንግድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ መሆኑን የኬንያ የግብርና ሚኒስትሩ ፒተር ሚኒያ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ፒተር ሙንያ በስምምነቱ መሰረት ፤ ናይሮቢ ታዋቂ የሆነውንና በሶማሊያውያን ተወዳጅ የሆነው ጫት ወይም ሚራ የተባለውን ለስላሳ የአደንዛዥ እጽ ቅጠል ወደ ውጭ መላክ የምትጀምር ሲሆን ሶማሊያ በበኩሏ የአሳ እና ሌሎች ምርቶች ትሸጣለች ብለዋል፡፡
ስምምነቶቹ በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈረሙም ተናግረዋል ሚኒሰትሩ፡፡
ሁለቱ ሀገራት በማክሰኞ በናይሮቢ ከሚካሄደው አህጉራዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የአቪዬሽን ስምምነት እንደሚያጠናቅቁም ገልጸዋል፡፡
የማሻሻያ እርምጃው የመጣው የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባለፈው ሀሙስ አዲስ በተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሹመት ስነስርዓት ላይ ከተገኙ በኋላ ነው፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ በበዓለ ስሜቱ ላይ ባደረጉት ንግግር "ሰላምና የበለጸገች የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ማየት የሁሉም ኬንያዊ ህልም ነው" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
"በኬንያ ያሉ ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ፣ ሁላችንም በኢኮኖሚ እንድንጠቀም እና አብረን እንድንበለጽግ ከእናንተ ጋር ለመስራት በጉጉት እንጠባበቃለን" ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
በፈረንጆቹ በመጋቢት 2020 የተጣለው እገዳ በቀን ከ50 ቶን በላይ የሚገመት የኬንያ ጫት ዋጋ ወደ ስድስት ሚሊዮን ሽልንግ (50 ሺህ ዶላር) እንዲወርድ እንዲወርድ ማድረጉን በማዕከላዊ ኬንያ የሚገኘው የኒያምቤን ሚራ ነጋዴዎች ማህበር ሊቀመንበር ኪምቲ ሙንጁሪ ተናግረዋል።
ኬንያ ወደ ሶማሊያ የምትልከው 13 ቢሊዮን ሽልንግ (ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ) በ2021 ወደ አፍሪካ ከላከቻቸው አጠቃላይ ምርቶች ውስጥ አምስት በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚይዝም የሀገሪቱ መንግስት መረጃ ያመለክታል፡፡
እናም የአሁኑ ስምምነት ሻክሮ ነበረውን የሀገራቱ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማሻሸል በዘለለ ሀገራቱ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ተብለዋል፡፡ 680 ኪሎ ሜትር (420 ማይል) የመሬት ድንበር የሚጋሩት ኬንያ እና ሶማሊያ ለረዥም ጊዜ በዘለቀው የድንበር ውዝግብ ምክንያት ግንኙነታቸውን በሚፈለገው ደረጃ ሳያጠናክሩ የቆዩ ሀገራት መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ናይሮቢ በሞቃዲሾ በማዕከላዊ መንግስት እውቅና ያልተሰጠውን ተገንጣይ የሶማሊላንድ የፖለቲካ አመራር ማስተናገዷን ተከትሎ በሀገራቱ መካካል ነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በታህሳስ 2020 መቋረጡ ሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ባሳለፍነው ወርሃ ነሃሴ 2021 የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብሌ ከኬንያታ ጋር ሲነጋገሩ ግንኙነታቸውን ለማደስ ተስማምተው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡