ህወሓት በኬንያ ለሚደረገው“ድርድር” የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን አስታወቀ
ህወሓት የኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቅረበት ምቾት እንዳልሰጠው ገልጿል
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው እለት በተወካዮች ም/ቤት በቀረቡበት ወቅት ከህወሐት ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል
ህወሓት በኬንያ መንግስት በተጠራው ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን የድርጅቱ ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሐት መካከል ድርድሮች እንዳሉ በተለያየ መንገድ ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት ምንም አይነት ድርድር አለመጀመሩን በተጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እየተካሄደ ስለሚባለው ድርድር ለህዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ምላሽ “ከህወሐት ጋር ወደ ጦርነት የተገባው በይፋ ነው ድርድሩም የሚካሄደው በይፋ ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከህወሐት ጋር ድርድር የሚደረገው የምንፈልጋቸው ሲሟሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ “በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ከህወሐት ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል” ለህዝብ እንደራሴዎቹ ግልጽ አድርገዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሐቱ ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በኬንያ መንግስት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸው አስታውቀዋል፡፡
ሊቀ መንበሩ ይህን ያሉት የሚደረጉ የሰላም ድርድሮችን በማስመልከት የትግራይ አቋምን ለማሳወቅ ፤ ለአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበርና የሴናጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል፣ ለኬንያው ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ፣ ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን እና ለታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን እንዲሁም የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተናንት ማምሻውን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ነው ፡፡
ሊቀ መንበሩ በጻፉት ደብዳቤ ለምን እንደሆነ ግልጽ ባያደርጉም “ሚስጥራዊ ስምምነቶችን ለማድረግ ዝግጁ አይደለንም” ብለዋል፡፡
ሊቀ መንበሩ የአህጉሪቱ ተቋም የሆነው አፍሪካ ህብረት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዝምታን መምረጡ፤ ከተቋሙ መርሆች በተቃራኒ ለመቆሙ ማሳያ ነው የሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
በዚህም የትግራይ ህዝብ እና የሚመሩት ድርጅት በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያላቸውን አመኔታ ለመመለስ እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡
ለሰላም ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን ለመጓዝ ያለን ዝግጁነት የምናምንባቸው መርሆቻችን ዘንግተን እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆን የተቀበልነው ለአፍሪካ ህብረት መርሆች እና ለሽማግሌዎች ባለን ክብር መሆኑ ሁሉም ሊያውቀው ይገባልም ብለዋል፡፡
ደብረጽዮን “ይህ ሲባል ተወካዩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያላቸው ቅርበት የትግራይ ህዝብ ሳያስተውለው ቀርቶ አይደለም” ሲሉም በኦባሳንጆ አዳራደሪነት ያላቸውን እምነት እምብዛም እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡
ከኦባሳንጆ በተቃራኒ ለታንዛኒያ እና ኬንያ መሪዎች ያላቸው ክብር እና ምስጋና ከፍ ያለ መሆኑም በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡
“በታንዛኒያ መንግስት እንተማመናለን እንዲሁም የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ለኢትዮጵያ ሰላም እያደረጉት ያለውን ጥረት እናደንቃለን”ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን “የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መርህ ላይ ተመሮኮዘና አካታች ሆነ የአደራዳሪነት ሚና” እናደንቃለን ብለዋል፡፡
በኬንያ ፕሬዚደንት መሪነት የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በናይሮቢ ለመገናኘት ለተደረሰው ስምምነት ተገዥ መሆቸውን የገለጹት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ህወሓትን የሚወክሉ ተደራዳሪዎች በቅረቡ ወደ ናይሮቢ ለመላክ መዘጋጀታቸውም አስታውቋል፡፡
ህወሓት በኬን መንግስት አመቻችነት እና አስተናጋጅነት በሚካሄደው ድርድር ላይ ለመገናኘት መስማማቱንም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
በሰላም ሂደቱ በኬንያው መንግስት መሪነት እንደ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፣የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያደርጉት ተሳትፎ በደስታ እንቀበላለን ሲሉም አክለዋል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ያለው ግጭት ሰለማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ የአፍሪካ ህብረትም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡