በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 50 የሚሆኑ ሹፌሮች በታጣቂዎች ታገቱ
ገርበ ጉራቻ አካባቢ ልዩ ስሙ አሊደሮ በሚባል ስፍራ ከ30 በላይ ከሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው መታገታቸውን የአይን እማኞችና ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ
ታጣቂዎች ለአገቷቸው ሰዎች ማስለቀቂያ ቤተሰባቸውን እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ ነው ተብላል
ቅዳሜ ሰኔ 10፤ 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ ልዩ ስሙ አሊደሮ በሚባል አካባቢ ከ50 በላይ ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው መታገታቸውን የአይን እማኞችና ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ-ጎጃም-ጎንደር መስመር ተፈጽሟል የተባለው እገታ 31 የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስጥ የነበሩ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው።
የአይን እማኞች ከ50 በላይ ሰዎች መኪናቸውን እንዲያቆሙ ተደርገው በታጣዊቆች እንደተወሰዱ ተናግረዋል። 20 እንደሚሆኑ የተገመቱት ታጣቂዎች በመተኮስ ሹፌሮችና ረዳቶች እንዲወርዱ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
ከእገታው የተረፈው እንቻለው የተባለ የአይን እማኝ (ረዳት) ከገርበ ጉራቻ ወጣ ብሎ ባለው ዳገታማ አካባቢ እገታው መፈጸሙን ለአል ዐይን ገልጿል።
በተለምዶ ኦባማ በሚባል አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ አትክልት ጭነው ወደ ደ/ማርቆስ ሲመጡ ጠዋት 12 ሰዓት ላይ እገታው መፈጸሙን ተናግሯል።
ለመተኛት እንዲመቸው ከላይ በሸራ በተሸፈነ የጭነት ቦታ ላይ በመተኛቱ ከእገታው መትረፉን የተናገረው እንቻለው፤ “ደገም” የተባለ ኬላን እንዳለፉ ጥቃቱ መሰንዘሩን ገልጿል።
ሸኔ የተባሉት ታጣቂዎች እገታውን መፈጸማቸውን የሚናገረው ረዳቱ፤ የእሱን ሹፌር ጨምሮ ከ40 እስከ 50 የሚገመቱ ሰዎች ታፍነዋል ይላል።
“ከፊታችን መኪኖች ነበሩ። ወደ 10 ሚኪና ነበር። ከኋላ የነበሩት ወደ አዲስ አበባ ዞረው ለመመለስ እየሞከሩ ነበር። ሲዞሩ መንገድ ተዘጋ። ሁሉም ለመዞር ሞከረና ተዘጋ። ከፊት ለነበሩት ከኋላ ተዘጋባቸው። ከዛ ተኩስ ልውውጥ ተጀመረ። [ታጣቂዎች] መተኮስ ጀመሩ። ለማስደንበርና ለማስፈራራት ነው ተኩስ የጀመሩት። ከእኔ ጋር አብሮ የነበረው ረዳት ውስጥ ተደብቀን ስለነበር ተረፍን” በማለት ድርጊቱን ገልጿል።
ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን ይዘው በስተግራ በኩል መታጠፋቸውን የአይን እማኙ ተናግሯል። ተኩሱን ሰምተው ስፍራው ላይ የደረሱት የጸጥታ ኃይሎች (ኬላ ላይ የነበሩ መከላከያዎች) አጋቾቹ በመኪና እንደሄዱ እንደነገሯቸውም አክሏል።
እንቻለው የስራ ባልደረባው ታጋች ሹፌር ቤተሰቦች 500 ሽህ ብር በማግስቱ እሁድ ዕለት እንደተጠየቁና ለመከፈል ሲንቀሳቀሱ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውንም ለአል ዐይን ተናግሯል።
“እየተደራደሩ ነበር። 500 ሽህ ብር ተጠይቀው ሊከፍሉ ነበር። ብሩን ሊያስገቡ ሲሉ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር ከፍ አደረጉባቸው። እንደሚከፍሉ እርግጠኛ ሲሆኑ ወደ አንድ ሚሊዮን አደረጉት” በማለት ታጣዊዎችና የታጋች ቤተሰቦች የነበራቸውን የስልክ ልውውጥ ጠቅሷል።
አብዛኞቹ ታጋቾች የደ/ማርቆስ (ምስራቅ ጎጃም) አካባቢ ተወላጆች ሲሆኑ የተጠየቀውን አንድ ሚሊዮን ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመሙላት ከማህበረሰቡ እያሰባሰቡ ነው። የታጋቾች ጓደኞችና ቤተሰቦቻቸው ፌስቡክን በመሰሉ ማህበራዊ የትስስር ገጾች ሳይቀር የባንክ ደብተር ከፍተው ገንዘብ እያሰባሰቡ ነው።
ለራሱና ለታጋች ወንድሙ (አብሮ አደግ ጓደኛው) ደህንነት በመስጋት ማንነቱን መጥቀስ ያልፈለገ ሹፌር “ሰርቶ መብላት ፈተና ሆኗል” ብሏል።
“ሹፌር አሁን ባለው ሁኔታ በአራቱም አቅጣጫ ሰርቶ መብላት እየቻለ አይደለም። ኃላፊነት አለ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ አለ፣ ቤተሰብ የሚረዳ አለ፣ ልጅ ያለው አለ። በዚህ ምክንያት የእኔ ጓደኞች 50፤ 60 የሚሆኑ ሹፌሮች ስራ ፈተው ቁጭ ብለዋል፤ ይህንን ፍራቻ። የታገተው ልጅ ደካማ እናቱ እንጀራ ጋግራ፤ ሰርታ ነው መንጃ ፈቃድ ያወጣው። ቤተሰቦቹን የሚረዳ ልጅ ነው። አይደለም አንድ ሚሊዮን ብር ሁለት ሦስት መቶ ሽህ ማግኘትን አስቸጋሪ ነው” በማለት ሁኔታውን ገልጿል።
እሁድ ጠዋት (ከእገታው ማግስት) “አንድ ሚሊዮን ብር ስትከፍሉ እንለቀዋለን” መባላቸውን የተናገረው ሹፌሩ፤ አል ዐይን በስልክ ሲያገኘው ከማህበረሰቡና ከሹፌሮች ገንዘብ እያሰባሰቡ በነበረበት ቅጽበት ነው።
ታጣዊዎቹ የጊዜ ገደብ ሳይሰጡ ገንዘቡ እንዴት እንደሚላክ እንደውላለን ማለታቸውን በታጋቹ አስደውለው መልዕክት አስተላልፈዋል ብሏል።
ከአዲስ አበባ-ጎጃም መስመር ለደህንነት በማስጋቱ በምሽት የሚደረግ ጉዞ ከዓመት በፊት ቆሟል። በመስመሩ ተመሳሳይ እገታ የሚፈጸም ሲሆን፤ ከወራት በፊት ሹፌሮች በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ በደ/ማርቆስ የስራ ማቆም አድማ መመታቱን አል ዐይን መዘገቡ የሚታወስ ነው።
የአይን እማኙ እንቻለው በታጣቂዎቹ ቢያዝ ኖሮ እጣ-ፈንታው ሞት እንደሚሆንም ይናገራል። “ብያዝ ኖሮ ቤተሰቦቼ የመክፈል አቅም ስሌላቸው፤ ወይ ማምለጥ አሊያም ሳመልጥ መገደል ብቻ ነው አማራጬ” በማለት ከሞት አፋፍ ተርፎ “ለሀገሩ” መብቃቱን ይናገራል።
በጉዳዩ ላይ አል ዐይን ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለ እገታውን መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ተናግሯል።