ታግቶ የነበረ ሹፌር መገደሉን ተከትሎ በደብረ ማርቆስ ከተማ ነጋዴዎች አድማ መቱ
ገብረ ጉራቻ አካባቢ ታግቶ ነበር የተባለ ሹፌር መገደሉን ተከትሎ ነው በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ የተገደበው
ከጎጃም አዲስ አበባ መስመር ባለፉት ወራት “ሸኔ” በተባሉ ታጣቂዎች ሰዎች መታገታቸው ቁጣን ቀስቅሷል
በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ ነጋዴዎች የስራ ማቆም አድማ መትተዋል።
ከሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ኩዩ ወረዳ ገብረ ጉራቻ አካባቢ ለአንድ ወር ያህል “በሸኔ” ታግቶ ነበር የተባለ ሹፌር መገደሉን ተከትሎ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ መገደቡን ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ትናንት ህዳር 29 የሹፌሩን መገደል አብሮ ታግቶ ነበር የተባለ ሰው ካረዳ በኋላ ለቀስተኛውና ነዋሪዎው ወደ በከተማዋ ወደሚገኘው ንጉስ ተ/ኃይማኖት አደባባይ በማምራት ፍትህን ጠይቋል።
ዛሬ ህዳር 30፤ በከተማዋ የንግድ መደብሮች ሙሉ ለሙሉ የተዘጉ ሲሆን ትራንስፖርትና ሆቴሎች ደግሞ በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ነው ተብሏል።
ባንኮች የተወሰኑት ከሰዓት በኋላ ቢከፍቱም የዘጉ ስለመኖራቸውም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የከተማው ነዋሪ "ሱቆች፣ ገበያዎች ተዘግተዋል። የትራንፖርትና የሰው እንቅስቃሴ ግን አለ። ሆቴሎችም በከፊል ክፍት ናቸው”ብለዋል።
የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ “ህዝባዊ እምቢተኝነት” ነው ያለችው አይንአዲስ ዋለልኝ የተባለች የህጻናት የልብስ መደብር ባለቤት እሷም ሱቋን እንደዘጋች ተናግራለች።
“የወገኖቼ ደም የእኔም ደም ስለሆነ ነው። በመንገድ [ከማርቆስ አዲስ አበባ] ሽፍታ፣ ኦነግ ሸኔ በሚል ወገኖቻችን እየታገቱ ነው፤ እተገደሉ ነው። አንድ ሚሊዮን ብር ክፈሉ፣ ሁለት ሚሊዮን ብር ክፈሉ እተባሉ ነው። በገዛ ሀገራችን ወጥተን መግባት አልቻልንም። ወገኖቻችን እያለቁ ነው” ስትል በምሬት ተናግራለች።
አይናዲስ መፍትሄ ካልመጣ “ህዝባዊ እምቢተኝነቱ” እንደሚቀጥልም ተናግራለች።
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገና ሱቁን እንደዘጋ የነገረን ነጋዴ ሰላም ከሌለ ሁሉ ነገር ወና ነው ብሏል። አጋቾች በነፍስ ወከፍ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ መሆኑንም ተናግሯል።
“ህዝቡ የሚፈልገውን መንግስት ያውቃል። ሰርተን እንድንበላ፤ ወጥተን እንድንገባ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ” ብሏል።
በደብረ ማርቆስና በምስራቅ ጎጃም የመንቀሳቀስና ደህንነት ስጋት መኖሩን የነገሩን ነዋሪ በሁኔታው “አዝነናል” ብሏል።
“አሳዛኝ ነው። ህዝቡ ለመንግስት ግብር የሚከፍለው ሰላሙንና ደህንነቱን እንዲጠብቅለት፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ እንዲሰራ ነው። ነገር ግን ያ እየሆነ አይደለም። በሀገርሽ ላይ ህግ ባለበት፣ መንግስት ባለበት ላይ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ አንድ ሚሊዮን ብር ክፈይ [ትባያለሽ] ለሽፍታ አንድ ሚሊዮን ብር ከፍለሽ ለመንግስትም ግብር ከፍለሽ እንዴት ነው የሚኖረው?” በማለት አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የአካባቢው ወጣት ሁኔታውን ገልጿል።
ነጋዴዎች አደማውን የመቱት እንደ እቁብ ያሉ ማህበራዊ አደራጃጀታቸን ተጠቅመው ሳይሆን እንደማይቀር ሰምተናል።
ለእርምጃው በዋናነት የደህንነት ዋስትና መጥፋቱ ምክንያት ሆኖ ተነስቷል።
“ከወገናችን ሞት ምንም አይበልጥብንም” ያለችው አይንአዲስ ለነጋዴዎች “ድምጻችንን ለማሰማት ትንሹ እርምጃችን ነው” ብላለች አይንአዲስ።
ባለፉት ወራት በርካታ ሹፌሮችና መንገደኞች መታገት፣ ግድያ፣ ተሽከርካሪዎችን ማቃጠል እንደበረታ ነዋሪዎች ጠቅሰዋል። በአካባቢው ከመንግስት ጠብ ያለ መፍትሄም ሆነ እርምጃ አለመወሰድ ቁጣ እንደቀሰቀሰ ተነግሯል።
ዛሬ የከተማዋ አስተዳደር ወኪሎች ሰልፍ የወጡና አድማ የመቱ ሰዎችን ሰብስበው ስለማናገራቸው ሰምተናል።
አመራሮቹ “ችግሩ ከእኛ የተሻገረ ነው” እንዳሏቸው እና ኮሚቴ መርጦ የክልሉንና የፌደራሉን መንግስት ለመፍትሄ እንደሚጠይቅ በስብሰባው የተሳተፉ አንድ ነዋሪ ነግረውናል።
መንግስት አጋቾችን በሚጠቀሙበት ስልክ፣ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢና የማስለቀቂያ ገንዘቡ እንዲተላለፍ በሚጠይቁበት ባንኮች ያሉ መረጃዎችን አሰባስቦ እርምጃ እንዲወስድ ነዋሪዎቹ ተማጽነዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ ይትባረክ አወቀ የኦሮሚያ ክልል የመንገዱን ሰላምና ደህንነትን እንዲጠብቅ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ከክልሉ አቅም በላይ ከሆነ ፌደራል መንግስት መግባት አለበት ያሉ ሲሆነ ችግሩን ለመፍታት የተወሰደው እርምጃ አጥጋቢ አይደለም ብለዋል።
የሚፈጠሩ ችግሮችን ለአካባቢው አስተዳደር እንደሚያሳውቁ የተናገሩት ከንቲባው መስመሩ እስከ ሱዳን ድረስ የሚያደርስ ስለሆነ መንግስት ተገቢውን ጥበቃ መስጠት አለበት ብለዋል።