የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ 47 የክልልና ሃገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው እንደሚሳተፉም ይጠበቃል
በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመራጮች ካርድ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከ1987 ዓ.ም አንስቶ ምርጫን በማድረግ ላይ ስትሆን 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የፊታችን ግንቦት መጨረሻ እና ሰኔ መጀመሪያ ላይ እንደሚካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።
በዘንድሮው ምርጫ ላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመራጮች ካርድ ያወጣሉ የሚል እቅድ አስቀምጦ ወደ ስራ መግባቱንም ነው ምርጫ ቦርድ ለአል ዐይን አማርኛ ያስታወቀው።
የአጠቃላይ ምርጫው የመራጮች ምዝገባ በመጪው ሳምንት ማለትም ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወንም በቦርዱ የወጣው የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል፡፡
ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ምዝገባውን ለማከናወን በሚያስችለው ዝግጅት ላይ መሆኑንም አስታውቋል።
በምርጫው 47 የክልል እና አገር አቀፍ ፓርቲዎች እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን 50 ሚሊዮን ዜጎች የሚፈልጉትን ፓርቲ መምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ እንደሚወስዱ ነው ቦርዱ የገለጸው፡፡
በ2007 ዓ.ም በተካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ 36 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ካርድ በመውሰድ በምርጫው የተሳተፉ ሲሆን 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ብዙ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የ2002 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ 63 ፓርቲዎች ሲሳተፉ 31 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ሠበው ድምጽ ሰጥተዋል።
በአንጻራዊነት ዝቅተኛ ፓርቲዎች ቢሳተፉበትም የማይረሱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በተስተናገዱበት የ1997 ዓ.ም 3ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ 34 ፓርቲዎች ሲሳተፉ 21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የመራጮች ካርዳቸውን ወስደው በምርጫው ተሳትፈዋል።
እንዲሁም በመጀመሪያው የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ በ1987 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን በዚህ ምርጫ ላይ 46 ፓርቲዎች ሲወዳደሩ 21 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው እንደተሳተፉ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።