“ገዢው ፓርቲ የዘንድሮውን ምርጫ የማሸነፍ እድል የለውም” እናት ፓርቲ
“ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት የምዕራባዊያን ርዕዮተ ዓለም ቤተ ሙከራ ነበረች” ሲሉም ገልጸዋል
“የጎሳ ፖለቲካ ሊያበቃ ይገባል” ሲሉ የእናት ፓርቲ ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ ተናግረዋል
ከሦስት ወር በኋላ እንደሚካሄድ ቀን ለተቆረጠለት 6ኛው አገራዊ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አስመዝግበው የምረጡን ቅስቀሳቸውን በማድረግ ላይ ናቸው።
አል ዐይን በዘንድሮው ምርጫ ከሚሳተፉ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ከሆነው እናት ፓርቲ ጋር ስለ ቀጣዩ ምርጫ እና ስለ ፓርቲው ዝግጅት ቆይታ አድርጓል።
ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ እናት ፓርቲ በዘንድሮው ምርጫ ከአፋር ፣ ሶማሊ እና ጋምቤላ ክልሎች ውጭ በተቀሩት ለክልል እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ይወዳደራል።
580 ዕጩዎችን ያስመዘገበው እናት ፓርቲ በዕጩዎች ብዛት ፓርቲው ከብልጽግና እና ኢዜማ ቀጥሎ ሦስተኛ ነው፡፡
ፓርቲው በአጭር ጊዜ እውቅና አግኝቶ እንዴት ብዙ እጩዎችን ማስመዝገብ ቻለ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም “አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አገሩን የሚወድ ነገር ግን ዝምታን የሚመርጥ ነው” ያሉት ዶ/ር ሰይፈስላሴ “የእኛ ፓርቲ ትኩረት ይሄ ማህብረሰብ ነው ፤ ለዛ ነው በአጭር ጊዜ የተሳካልን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት የምዕራባዊያን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ቤተ ሙከራ ሆናለች” የሚሉት ዶ/ር ሰይፈስላሴ ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነው ደርግ የሶሻሊዝም ስርዓት፣ ቀጥሎም በምትኩ የተተገበረው የጎሳ ፖለቲካ የሙከራው አካላት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት ለየት የሚያደርገው “የጎሳ ፖለቲካ እና የአንድነት ፖለቲካ የሚፋተጉበት” መሆኑን ገልጸው ነገር ግን “ህዝቡ በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ተጨማሪ ጉዳትን ላለማስተናገድ ሲል ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑና የአንድነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ፓርቲዎችን እንደሚመርጥ” በእርግጠኝነት ተናግረዋል። “የጎሳ ፖለቲካ እዚህ ላይ ሊያበቃ ይገባል” ሲሉም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት “በእኛ እና እነሱ ፖለቲካ ስትታመስ ቆይታለች” የሚሉት ዶ/ር ሰይፈስላሴ ይህ የሆነው ለአገር በቀል የአስተዳደር ዘዴዎች ትኩረት ባለመሰጠቱ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ገዢው የብልጽግና ፓርቲም የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ መሆኑን በመግለጽ “ገዢው ፓርቲ የዘንድሮውን ምርጫ የማሸነፍ እድል የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።
እናት ፓርቲ አሁን ባለው የዝግጅት መጠን በምርጫው አሸንፎ “ብቻውን መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ባያገኝም ከሌላ የተሻለ ድምጽ ካገኘ ፓርቲ ጋር በመጣመር መንግስት እንመሰርታለን” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቋሚ እውቅና ከተሰጠው አንድ ወር የሆነው እናት ፓርቲ በጊዜ ጥበት ምክንያት በአፋር ፣ ሶማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች እጩዎችን ማስመዝገብ እንዳልቻለ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት ገልጸዋል።
ይሁንና ፓርቲያቸው በማይወዳደርባቸው አካባቢዎች ያሉ የፓርቲው አባላት “ድምጻቸውን ኢትዮጵያዊነትን ለሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች እንዲሰጡ እንደሚያደርጉም” ተናግረዋል።
ፓርቲው በዘንድሮው ምርጫ ላይ ካስመዘገባቸው 580 እጩዎች መካከል 70 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ “ኢትዮጵያ በሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ብትመራ” የተሻለ እንደሚሆንም ፓርቲው ገልጿል።
በኢትዮጵያ አሁን ያለው “የኑሮ ውድነት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች ምንጫቸው የተሳሳተ ፖሊሲ ትግበራ ነው” የሚሉት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ኢትዮጵያ ለእርሻ ስራ ተስማሚ አፈር እና የአየር ንብረት እያላት “በምግብ እራስን ካለመቻላችን በተጨማሪ ግብርናችን አለመዘመኑ ያሳዝነኛል” ብለዋል፡፡