በአፍጋኒስታን በመስጊድ አቅራቢያ በደረሰ ፍንዳታ እስካሁን 50 ሰዎች ሞቱ
አይ ኤስ አይኤስ በአፍጋኒስታን ለደረሱ ጥቃቶች ሃላፊነቶችን ወስዷል
ታሊባን አሜሪካ ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩ ይታወሳል
በሰሜን ምስራቅ አፍጋኒስታን ቀንዱዝ ከተማ መስጊድ አቅራቢያ በደረሰው ፍንዳታ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ሀገሪቱን የተረከበው ታሊባን አስታወቀ፡፡
የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ በትዊተር ገጹ እንዳሰፈረው ፍንዳታው የደረሰው በሺያ መስጊድ አቅራቢያ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህ ፍንዳታም የሟቾች ቁጥር እስካሁን ባለው ሰዓት 50 የደረሰ ሲሆን 140 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸው ተገልጿል፡፡ በአደጋው ስፍራ የደረሱ እማኞች እንዳሉት የሟቾችም ሆነ የተጎጅዎች ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ እንዳላ በመስጊድ አቅራቢያ የደረሰውን ይህንን ፍንዳታ ለማጣራት ልዩ ቡድን ተቋቁሟል፡፡ ይህ ቡድንም አደጋው የደረሰበት ቦታ መድረሱንም ቃል አቀባዩ በትዊተር ገጹ አስፍሯል፡፡
የቁንዱዝ ከተማ ነዋሪዎች በመስጊዱ አቅራቢያ የደረሰው ፍንዳታ መስጊዱን መምታቱ ለመገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል፡፡
በሰሜን ምስራቅ አፍጋኒስታን ቀንዱዝ ከተማ መስጊድ አቅራቢያ ለደረሰው ፍንዳታ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል እንደሌለ ተገልጿል፡፡ ይሁንና በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲደርሱ የነበረ ሲሆን ለነዚህ ተደጋጋሚ ጥቃቶችም አይ ኤስ ኃላፊነቱን ይወስድ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የወጡ ፎቶዎች እንደሚሳዩት ደም ያለባቸው አስክሬኖች በወለል ላይ ታይተዋል፡፡ይሁንና እነዚህ ፎቶዎች በትክክል ማረጋገጫ አልተሰጣቸውም፡፡
የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍረጋስታን መወጣታቸውን ተከትሎ ለ20 አመታት ያህል የትጥቅ ትግል ገጥሞ የነበረው ታሊባን አፋጋኒስታንን ተቆጣጥሮ ቤተመንግሰት መግባቱ ይታወሳል፡፡