“የአሜሪካ የአፍጋኒስታን ቆይታ በአሳዛኝ ሁኔታ ነው የተቋጨው”- ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
የሁለት አስርታቱ የአሜሪካ ቆይታ “ትልቅ ኪሳራ” እንደነበርም ነው የገለጹት
ፑቲን ይህ ዋሽንግተን “ፍላጎቷን በሌሎች ላይ ለመጫን በመሞከሯ” የመጣ ነው ብለዋል
ለ20 ዓመታት የዘለቀው የአሜሪካ የአፍጋኒስታን ቆይታ “በሚያሳዝን ሁኔታ በሽንፈት” መጠናቀቁን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ፡፡
ፑቲን የሁለት አስርታቱ የአሜሪካ ቆይታ “ትልቅ ኪሳራ” እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ምዕራባውያን በሌሎች ላይ “የራሳቸውን እሴቶች ለመጫን” ያደርጋሉ የሚሉትን ጥረት ክፉኛ በመተቸት የሚታወቁት ፑቲን፤ የአፍጋኒስታኑ የዋሽንግተን ቆይታ “በአሳዛኝ ሁኔታ” መቋጨቱም የዚሁ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ሩሲያ የአሜሪካንን የአፍጋኒስታን ፖሊሲ ብዙ ጊዜ “ያልተገባ” በሚል ስትወቅስ ትደመጥ ነበረ እንደ ሞስኮው ታይምስ ዘገባ፡፡
የአሜሪካን ፍላጎቶች በአፍጋናውያን ላይ ለመጫን ይሞከር ነበር ያሉት ፑቲን ውጤቱ ሽንፈት ነው ሲሉ ተናግረዋል፤ ገፈቱ ለአፍጋናውያን ጭምር መድረሱን በመጠቆም፡፡
የትኛውንም ነገር ከውጭ ለመጫን አይቻልም ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
የ70 ዓመቱ ቭላዲሚር ቭላዲሚሮቪች ፑቲን ይህን ያሉት፤ የዘንድሮው የትምህርት ዓመት መጀመሩን በማስመልከት በምስራቃዊ ሩሲያ ቭላዲቮስቶክ ከተማ ተሰብስበው ለነበሩ ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ፑቲን ባሳለፍነው ሳምንት ሃገራቸው በአፍጋኒስታን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ ተናግረዋል፡፡