ድር እና ማሪሀን የተሰኙ የሶማሊያ ጎሳ አባላት ግጭት መነሻ መሬት ነው ተብሏል
በማዕከላዊ ሶማሊያ በተፈጠረ የጎሳ ግጭት 50 ሰዎች ተገደሉ፡፡
በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ በተፈጠረ የጎሳ ግጭት 55 ሰዎች እንደተገደሉ ተገልጿል፡፡
ማሪሃን እና ዲር በተሰኙ የሶማሊያ ጎሳዎች መካከል በተከሰተው በዚህ ግጭት ከሟቾች በተጨማሪ 155 ሰዎችም ቀላል እና ከባድ የአካል መጉደል አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ በሶማሊያ በተለያዩ መልኩ አለመረጋጋቶች የሚከሰቱ ሲሆን የጎሳ ግጭቶች፣ የአልሻባብ ጥቃቶች እና የመሬት ይገባኛል ግጭቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ለዲር እና ማሪሃን ጎሳዎች ግጭት መነሻ ነው የተባለው በአርብቶ አደሮች መካከል መሬት እና ውሃ ይገባኛል በሚል እንደተከሰተ ተገልጿል፡፡
ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጦር አስወጣለሁ ማለት እና የኢትዮጵያ ምላሽ
ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ቀናት የተከሰተው ይህ ግጭት አልሻባብን ለማጥፋ በተጀመረው ጥቃት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል በዘገባው ለይ ተጠቅሷል፡፡
የመንግስት የጸጽታ ሀይሎች ወደ ስፍራዎቹ ያመሩት ግጭቱ ከተባባሰ እና ከሁለቱም ጎሳዎች ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የጋልሙዱግ ክልል የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አህመድ ሽሬ እንዳሉት ከዚህ የጎሳ ግጭት ጀርባ በእርግጠኝነት አልሻባብ እጁ አለበት ብለዋል፡፡
አሁን እርስ በርስ ተገዳደሉ የተባሉት ዲር እና ማሪሃን ጎሳዎች አልሻባብ ከማዕከላዊ ሶማሊያ ለቆ እንዲወጣ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ናቸው ያሉት አማካሪው ወደ ግጭት የሚያስገባቸው ምንም ምክንያት እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ወይም አትሚስ ከቀጣዩ ታህሳስ ጀምሮ የቆይታ ጊዜው የሚያበቃ ሲሆን ሶማሊያ የዚህ ሰላም አስከባሪ የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም እየጠየቀች ትገኛለች፡፡
ይሁንና በሶማሊያ ያለው የኢትዮጵያ ጦር ከቀጣዩ ታህሳስ ወር በኋላ ለቆ እንዲወጣ ከስምምነት ላይ እንደደረሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የደህንነት አማካሪ ከሰሞኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በበኩሏ በአትሚስ ስር የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሀይል ቆይታው እስከ ቀጣዩ ታህሳስ ወር ድረስ ቢሆንም የኢትዮጵያ ጦር ለቆ እንዲወጣ ከሶማሊያ መንግስት ጋር እንዳልተነጋገረች አስታውቃለች፡፡