ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጦር አስወጣለሁ አለች
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የወደብ ስምምነት የማትሰርዝ ከሆነ በአመቱ መጨረሻ የኢትዮጵያን ጦር አስወጣለሁ ስትል ዝታለች
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለውን አልሸባብ ለመዋጋት በሶማሊያ 3000 የኢትዮጵያ ጦር ይገኛል
ሶማሊያ በሰላም ማስከበር የተሰማራውን የኢትዮጵያን ጦር አስወጣለሁ አለች።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የወደብ ስምምነት የሰኔ ወር ከመጠነቀቁ በፊት የማትሰርዝ ከሆነ በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደምታስወጣ የሶማሊያ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሁሴን ሼክ አሊ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ጊዜ ‘’ጠበኛም ወዳጅም’’ ልትሆን አትችልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአምስት ሀገራት የተውጣጣው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦር በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ የጸጥታ ስራውን ለሶማሊያ ጦር አስረክቦ እንደሚወጣ ቢያሳውቅም ሞቃዲሾ ግን ጦሩ እንዲቆይ ፍላጎት አላት፡፡
ህብረቱ በሰኔ ወር መጨረሻ አነስተኛ ቁጥር ያለው አዲስ የሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ ስፍራው እንደሚልክ ማስታወቁን ተከትሎ ሶማሊያ አዲስ በሚዋቀረው ጥምር ጦር ውስጥ የኢትዮጵያ ሰራዊት እንዳይሳተፍ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሮይተርስ ማብራርያ የሰጡት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ኦማርም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ሚንስትሩ ‘’አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንዲካተት መፍቀድ የማይታሰብ ነው’’ ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አልሸባብን ለማጥፋት መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈተችው ሞቃዲሹ የደህንነት ሁኔታዋ አሁንም አስተማማኝ የሚባል አይደለም፡፡
የደህንነት ባለሙያዎች እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኞች ሶማሊያ አሁን በምትገኝበት የጸጥታ ሁኔታ የኢትዮጵያ ጦር እንዲወጣ መጠየቅ ሁኔታዎችን የሚያባብስ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም የሶማሊያ የጸጥታ ሀይሎች ወቅታዊ አቋም የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት በመውጣቱ የሚፈጠር ክፍተትን ለመሙላት የሚያስችል አቅም የላቸውም ነው ያሉት፡፡
በሶማሊያ ከጂቡቲ፣ ብሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የተውጣጣ ከ5ሺህ-7ሺህ የሚገመት ጦር ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ 3ሺህ የሚሆነው ወታደር የኢትዮጵያ ነው፡፡
በጥር ወር ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ ከወደብ ጋር በተያያዘ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሞቃዲሾ ሰዎችን በእጅጉ አስቆጥቷል፡፡
ይህን ተከትሎም በሞቃዲሾ እና አዲስ አበባ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ መቃቃር ተቀይሯል፡፡
ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር በ72 ሰአታት ውስጥ ከሀገሪቱ ለቀው እንዲወጡ ያደረገች ሲሆን በሶማሊላንድ እና ፑንት ላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎችንም ዘግታለች፡፡
ኢትዮጵያ በበኩሏ በሶማሊላንድ ሃርጌሳ የሚገኘውን የቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ሙሉ አገልግሎት ወደሚሰጥ ኤምባሲ ማሳደጓ ተገልጿል።
በመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ የባህር ሀይል ማቋቋሚያ እና የንግድ ወደብ የምታገኝበት በምላሹ ለሀርጌሳ የሀገርነት እውቅናን እንደምትሰጥ መነገሩ ይታወሳል፡፡
ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ካልተወች ለንግግር ፈቃደኛ አለመሆኗን አስታውቃለች
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት በግልጽ ጥሳለች ያሉት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ይህ ስምምነት ካልተሰረዘ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን አትቀበልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ሌሎች ሀገራት ከሚያደርጉት የተለየ እንዳልሆነ እና የማንንም ሉዓላዊነት እንዳልጣሰች መግለጿ ይታወሳል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም በመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ አቋሟን እንዳልለወጠች መናገራቸው አይዘነጋም።