የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚረዱ መተግበሪያዎች
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የኤሌክትሮኒክስ መተግበሪያዎች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ያምናል
መተግበሪያዎቹ በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን የሙቀት መጠን ለማወቅ ይረዳሉ
አለማችን ካስመዘገበችው እጅግ ሞቃታማ ወቅት 94 ከመቶው ከፈረንጆቹ 2000 እስከ 2020 ባለው የተከሰተ ነው።
በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የካርበን ዳይ ኦክሳይድ መጠንም እጅግ እየጨመረ መሄዱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ እያስተናገደች ያለውን ፈተና በተለያዩ ሀገራት በተከሰቱ የድርቅ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎች ብናይም የየዕለት ለውጧን የሚያሳዩ የኤሌክትሮኒክስ መተግበሪያዎችም ተሰርተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ በሚከናወኑ ተግባራት የእነዚህ መተግበሪያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻል።
የካናዳው “ላይፍ አርክቴክት ሞኒተር” ድረገጽም በአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው ያላቸውን 6 መተግበሪያዎች አስተዋውቋል።
1. ISeeChange
በፈረንጆቹ 2010 የተቃወቀው “ISeeChange” በአለም ዙሪያ በየቀኑ ያሉ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን ያደርሳል። የመተግበሪያው ተጠቃሚዎችም በየአካባቢያቸው ያሉ ለውጦችን በማጋራ ውይይት እንዲደረግባቸው ያመቻቻል።
2. Earth-Now
የአሜሪካው የጠፈር አስተዳደር ናሳ በፈረንጆቹ 2012 ይፋ ያደረገው መተግበሪያ “Earth-Now” የሳተላይት መረጃዎችን በመጠቀም የምድርን አሁናዊ የአየር ሁኔታ ያሳውቃል። የምድርን ሙቀትም ሆነ የውቅያኖሶችን በበረዶ ግግር መሞላትና መቅለጥ በዚህ መተግበሪያ መመልከት ይቻላል።
3. Skeptical Science
በአውስትራሊያዊው ጆን ኩክ በፈረንጆቹ በ2007 ይፋ የተደረገው “Skeptical Science” የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረክ ነው። በዚህ መተግበሪያ በአለማቀፍ ደረጃ በዘርፉ አንቱታን ያተረፉ ሰዎች ጽሁፎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፥ በየእለቱ የሚታዩ ለውጦች ላይም ምክክር ይደረግበታል።
4. ClimateCounts
በፈረንጆቹ 2007 ይፋ የተደረገው “Climate Counts” መተግበሪያ ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚበረታታ ስራ የከወኑ ተቋማትን ደረጃ እያወጣ የሚያሳውቅ ነው። በመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ዶላር እያወጡ በዋነኞቹ በካይ ኩባንያዎች ላይ ጫና እንዲያደርጉም እድል ፈጥሯል። “Climate Counts” የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የግዙፍ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ዜጋ ተሳትፎ የሚሻ መሆኑን ያሳየና ስኬታማ ስራዎችን እየከወነ ያለ ነው።
5. EJAtlas
በስፔን ባርሴሎና የኡቶኖማ ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆቹ 2015 ያስተዋወቀው “EJAtlas” መተግበሪያ በአለማቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች የሚደርሰውን የአካባቢ ብክለት እና የማህበረሰብ ችግር የሚመዘግብና ይፋ የሚያደርግ ነው። በግድብ ግንባታም ይሁን በማዕድን ቁፋሮ ወቅት የሚደርሱ ጉዳቶችን እና የህብረተሰቡን ቅሬታ መዝግቦ ፍትህ እንዲሰፍን ይሰራል።
6. Greentech Media
በስኮት ካልቪና እና ሪክ ሮምሰን በ2007 ይፋ የተደረገው “Greentech Media” መተግበሪያ ከታዳሽ ሃይል ልማትና ሽያጭ ጋር የተያያዙ ትኩስ ዘገባዎች ይሰራጩበታል።
ሁሉም ከለኣይ የተጠቀሱት መተግበሪያዎች በማንኛውም ስማርት ስልክ የሚሰሩና በነጻ ከአፕ ወይም ፕሌይስቶር ላይ ልናወርዳቸው የምንችላቸው ናቸው።
ከነዚህም ባሻገር እንደ “Chasing Ice”፣ “iHurricane HD” እና “AlertMe Energy Map” ያሉ መተግበሪያዎችም የምድራችን ገጽታ እና ከባቢ አየር ለውጥ ለመቃኘት ያገለግላሉ።