57ኛ ዓመት ‘የአፍሪካ ቀን’ ዛሬ እየተከበረ ነው
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ 57 ዓመታት ቢቆጠሩም አሁንም የአህጉሪቱ ዉስብስብ ችግሮች አልተፈቱም
“በመድበለ ፓርቲ ስርዓት እና የዲሞክራሲ መርሆዎች ሰበብ ጠባብነት እና ጎሰኝነት በአፍሪካ ተንሰራፍቷል” ሙሳ ፋኪ
57ኛ ዓመት ‘የአፍሪካ ቀን’ ዛሬ እየተከበረ ነው
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) የተመሰረተው የዛሬ 57 ዓመት ልክ በዛሬዋ ቀን ግንቦት 17/ 1955 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ ዛሬ 57 ዓመቱን ደፍኗል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ‘የአፍሪካ ቀን’ በመባል የሚታወቀውን 57ኛ የምስረታ በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡
ሲሪል ራማፎዛ እንዳሉት ምንም እንኳን በርካታ ችግሮች ቢኖሩባቸውም የአፍሪካ ሀገራት አስደናቂ በሆነ መንገድ ኮሮናን ለመከላከል አንድ ላይ መቆም ችለዋል፡፡ ይሄም ዓለም አቀፍ አድናቆትን እንዳስገኘ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ከአባል ሀገራት ሀብት የማሰባሰብ ተግባራትም አስደናቂ ናቸው ብለዋል ፕሬዝዳንት ራማፎዛ፡፡ ይሄም “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ ነው” ያሉት የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር፣ ”የአሁኑ ትብብራችን የአፍሪካን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል ለምናደርገው ጥረት መነሳሳትን የሚፈጥር ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሲሪል ራማፎዛ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ደግሞ የህብረቱን 57ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት ባወጡት መግለጫ፣ እንደ አፍሪካ ቀን ተደርጎ የሚቆጠረው የህብረቱ የምስረታ ቀን ፣ እንደ ሁሉም አስፈላጊ ክብረ በዓላት ፣ የደስታ ብቻ ሳይሆን የኩራት ፣ የነፀብራቅ እና የማሰላሰያ በዓልም ነው ብለዋል።
ከ 57 ዓመታት በፊት አፍሪካ በቅኝ ግዛት ወረራ ምክንያት የተናጋባትን አንድነት ለመመለስ የሚያስችላትን የጋራ መሠረት ጥላለች ያሉት ሙሳ ፋኪ፣ ከዚህ በኋላ አህጉሪቱ በጋራ ትብብር ራሷን ከቅኝ ግዛት እና የአፓርታይድ ስርዓት ማላቀቅ መቻሏን አውስተዋል፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ አንድነቷንከማስጀመር በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እድገቶችን ብታስመዘግብም በነዚህ ዘርፎች ግልጽ ድክመቶች እና መዘግየቶች መኖራቸው የማይደበቅ ሀቅ እንደሆነም ሙሳ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡
አፍሪካ የአህጉሪቱ መስራች አባቶች እንደነበራቸው ህልም የነፃነት ፣ የሰላም ፣ የብልጽግና እና የስኬት አህጉር ሆናለችን? አፍሪካዊያን አንድነታቸውን ጠብቀው በመደጋገፍ የእድገት ጉዞ እያደረጉ ነውን? አፍሪካ ካላት ሰፊ እምቅ እና ሕጋዊ ምኞት ጋር የተስተካከለ ቦታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አግኝታለችን? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ድረስ የአህጉሪቱን ህዝብ ያለማቋረጥ የሚረብሹ ጥያቄዎች መሆናቸውንም ሙሳ ፋኪ አንስተዋል፡፡
አፍሪካ ምንም ያህል ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ እምቅ አቅም እና ወጣት የሰው ኃይል ቢኖራትም ፣ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት የህዝቦቻቸውን ብልጽግና ማረጋገጥ ተስኗቸዋል፡፡
እንደ ትምህርት ፣ ጤና እና ደህንነት ያሉ ቁልፍ ዘርፎች በአብዛኛው በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው፡፡ ሙሳ ፋኪ እንደሚሉት በመድበለ ፓርቲ ስርዓት እና ለብዙ ጊዜ ተከልክለው በቆዩ የዲሞክራሲ መርሆዎች ሰበብ ጠባብነት እና ጎሰኝነት በአፍሪካ ይበልጥ ጎልተው ይታያሉ።
በሽብርተኝነት እና ጎሳ (ዘር) እና ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ከሚፈጠሩ ግጭቶች ጀምሮ በምርጫ እና ድህረ ምርጫ ወቅት እስከሚፈጠሩ ቀውሶች ድረስ አፍሪካ አለመረጋጋት የሚታይባት ብቻ ሳይሆን የወደፊት እጣ ፋንታዋን ለመተንበይም የምታስቸግር አህጉር ነች፡፡
አህጉሪቱን ከውስብስብ ችግሮቿ ለማውጣት ዋነኛው መፍትሄ ደግሞ በየአከባቢው ላይ ያሉ ጠመንጃዎች ዝም ማለታቸውን ማረጋገጥ እንደሆነ እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ገልጸዋል፡፡
ህብረቱን በማጠናከር የ2063 ግቦችን ለማሳካት መረባረብ ያስፈልጋል ሲሉም ሙሳ አብራርተዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ ማሃማት
የመላው ዓለም ፈተና የሆነውን እና በአፍሪካም በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም በተባበረ ክንድ ለመመከት መስራት እንደሚገባ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር አሳስበዋል፡፡
ለ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) እና አስከፊ መዘዞችን ለመቆጣጠር ብቸኛው መንገድ የምግብ ፍላጎታችንን በማረጋገጥ ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስራዎችን በመፍጠር በአሁኑ ጊዜ ለከባድ ወረርሽኝ እና ለሌላ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካዊ ዜጎችን መታደግ እንደሆነ ሙሳ ጠቁመዋል፡፡