ደቡብ ሱዳን በ12 ቀናት ውስጥ የሽግግር መንግሰት መመስረት አለባት-የአፍሪካ ህብረት
ደቡብ ሱዳን በ12 ቀናት ውስጥ የሽግግር መንግስት እንድትመሰርት የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ
በአፍሪካ አጠቃላይ ወቅታዊ የሰለምና ጸጥታ ሁኔታ ላይ መግለጫ የሰጡት የህብረቱ የሰለምና ጸጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር አምባሳደር ኢስማኢል ቸርጊ እንደተናገሩት የተኩስ ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን መፍጠር በሚቻልበት ጉዳይ የአፍሪካ መሪዎች በሰፊው እየተወያዩ ነው፡፡
የህብረቱ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን በመላው አፍሪካ በሚገኙ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ከአህጉሪቱ መሪዎች ጋር መምከሩንም አምባሳደር ቸርጊ ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ በተመለከተ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ሀይሎች የሽግግር መንግስት እንዲመሰርቱ ከተሰጣቸው 100 ቀናት ውስጥ በቀራቸው 12 ቀናት፣ ቀድሞ በተስማሙት መሰረት የሽግግር መንግስት መመስረት እንዳለባቸው ህብረቱ የጸና አቋም መያዙን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ደቡብ ሱዳን ባለፉት 88 ቀናት የሽግግር መንግስቱን ለመመስረት የሚያስችሏትን ጉዳዮች አላከናወነችም፡፡ ከነዚህም አንዱ የሀገሪቱን የጋራ ብሔራዊ ጦር ማቋቋም ሲሆን እስካሁን በዚህ ረገድ ምንም የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የሀገሪቱ ክልሎች ስንት ይሁኑ የሚለውን ቁጥር የመወሰን ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይም ቢሆን በሁለቱ ዋነኛ ተቀናቃኞች መካከል ተቀራራቢ ሊባል የሚችል ስምምነት ላይ አልተደረሰም፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም በፈተና ውስጥ በምትገኘው ደቡብ ሱዳን የታየው የጥይት ድምጾች መቀነስ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከታዩ መልካም ለውጦች መካከል የሚጠቀስ እንደሆነ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በሌላ የምስራቅ አፍሪካ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ አምባሳደር ኢስማኢል ቸርጊ ሶማሊያን አንስተዋል፡፡ በተለይም በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልእኮ (አሚሶም) 1,000 ሰላም አስከባሪዎች ሀገሪቱን ለቀው እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱ ጦር አቅሙን እንዲያጠናክር ድጋፍ ይደረጋልም ብለዋል አምባሳደር ቸርጊ፡፡
አሁን ላይ በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ግጭት በማስተናገድ ላይ የሚገኙት የሰሜን አፍሪካና የሳህል ቀጣና ህብረቱ ከፍተኛ ትኩረት የሰጣቸው አካባቢዎች መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
በሊቢያ ጉዳይ ኮሚሽኑ ከተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ከሙሳ ፋኪ መሀመት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የመከረ ሲሆን የሀገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ህብረቱ በቅርቡ የሰላም አሰከባሪ ተልእኮ ወደ ሊቢያ ሊልክ እንደሚችል ቸርጊ ጠቁመዋል፡፡
የተባበሩትመንግስታት እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ እናደንቃለን ያሉት አምባሳደር ቸርጊ በሊቢያ ላይ ድርጅቱ የጣለው የጦር መሳሪያ ማእቀብ ሙሉ በሙሉ እንዲጸና የሁሉም ፍላጎት በመሆኑ በትብብር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከሰሀራ በታች የሚገኘውን የማሊ፣ ኒጀርና ቡርኪናፋሶ ግዛቶች የሚያካትተው የሳኸል ቀጣና የተለያዩ ጽንፈኛ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበት እና ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡
ይህ አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚካሄድበትም ሲሆን ባጠቃላይ የጥይት ድምጾችን ጸጥ ለማሰኘት ለመሳሪያ ግዢ የሚውል የገንዘብ ምንጭን ለማድረቅ በትኩረት እንደሚሰራ ቸርጊ ተናግረዋል፡፡
በሳኸል ቀጣና ላለው ቀውስ መሰረታዊ ምክኒያቱን አጥንተን ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ለህብረቱ አቅርበናልም ነው ያሉት፡፡
የህብረቱ ስብሰባ ለአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ ምንም ፋይዳ የለውም የሚለው ሀሳብ ሀሰት ነው ያሉት ቸርጊ፣ ለዚሁ ጉዳይ በአሁኑ 33ኛ ጉባኤ ህብረቱ በፊት ከመደበው 154 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ 10 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል ብለዋል፡፡
በማእከላዊ አፍሪካ ያለው ሁኔታ ደግሞ ተስፋ ሰጪ እንደሆነና ሀገሪቱ ወደ አንጻራዊ መረጋጋት እየመጣች እንደምትገኝ የገለጹት ቸርጊ በቅርቡ ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ቀውስ እንዳያገረሽ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ለምርጫው የሚውል ገንዘብ ህብረቱ በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
ለ20 ዓመታት ያክል የዘለቀው የዝምባብዌ ማእቀብ ኢ-ሞራላዊ እና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉ አምባሳደር ቸርጊ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በመሆኑም በሀገሪቱ ላይ የተጣለው ማእቀብ እንዲነሳ አጥብቀን እየሰራን ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ቸርጊ መግለጫቸውን ሰጥተው ከጨረሱ በኋላ ከተለያዩ ሀገራት ጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች የተነሱላቸው ሲሆን አብዛኛው ጥያቄዎች በሊቢያ ጉዳይ በሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች እና ህብረቱ ተልእኮውን በመፈጸም ረገድ ባለው አቅም እና ተነሳሽነት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ሙአማር ጋዳፊ ከተገደሉበት ጊዜ ጀምሮ መረጋጋት የተሳናት ሊቢያ፣ የቀውሷ ዋነኛ ምክንያት የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ሀገራት ከሊቢያ ሁለት ዋነኛ ተፋላሚዎች ጎን ተሰልፈው በሀገሪቱ ለዓመታት የዘለቀውን ውጊያ ማብቂያ የሌለው አድርገዋል፡፡ በዚህ ጣልቃ ገብነት የሚታሙ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትም አሉ፡፡ ይሁንና ህብረቱ እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም ምንም አይነት እርምጃ አልወሰደም ተብሎ ይታማል፡፡