በረራን መቆጣጠር የሚችል ብሔራዊ ኩባንያ መቋቋሙ የደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ያስችላል ተብሏል
ነጻነቷን ካገኘች 10 ዓመት የሞላት ደቡብ ሱዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የአየር ክልሏን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሯን የሀገሪቱ ባለስጣናት አስታወቁ፡፡
ሀገሪቱ ከሱዳን ነጻ የወጣችው በአውሮፓውያኑ 2011 ሲሆን ከ10 ዓመታት በኋላ በሱዳን አቪዬሽን ባለስልጣን የሚተዳደረውን የአየር ክልሏን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደምትችል ይፋ አድርጋለች፡፡ የደቡብ ሱዳን የአቪዬሽን ሚኒስትር ሜዱት ፒያር ዬል ዛሬ በጁባ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ መንግስት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራን መቆጣጠር የሚችል ብሔራዊ ኩባንያ ማቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም “በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር ጋር የተያያዘውን አነስተኛ የአየር ክልል የሚቆጣጠር ብሄራዊ ኩባንያ አቋቁመን ተጨማሪ በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሰማራት ዝግጁ” መሆናቸው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ቁጥጥሩ መጀመሩ የደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ የሚደግፍ መሆኑን እና ከሚያርፉ አውሮፕላኖች ገቢ ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡ በአውሮፓውያኑ 2023 ደቡብ ሱዳን የላይኛውን የአየር ክልል መቆጣጠር እንደምትችልም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት ሀገሪቱ በምድርም በአየርም ነጻነቷን ያረጋገጠች መሆኗ ለሕዝቡ ትልቅ ብስራት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ባደረጉት ስምምነት ለደቡብ ሱዳን የአየር ክልል ቁጥጥር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ካርቱም እና ጁባ አድርገውት በነበረው ስምምነት መሰረት ደቡብ ሱዳን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር አቅምን ስታጎለብት ሱዳን ስራውን አስረክባ ትወጣለች፡፡