ሱዳናውያን ለተቃውሞ የተሰበሰቡት አሁን ሀገራቸውን የሚመራው መንግስት እንዲቀየር ጥሪ ለማቅረብ መሆኑ ተሰምቷል
ሱዳናውያን ሰልፈኞች በመዲናዋ ካርቱም የሚገኘውን የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱን ሊቀ መንበር አብዱል ፋታህ አልቡርሃንን ቤተ መንግስት መክበባቸውን ገለጹ።
የሱዳን ዜጎች ዛሬ ሰልፍ እያደረጉ ያሉት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች እንደሆነም ነው የወጡ ፎቶዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የሚያመለክቱት።
ከተለያዩ የሙያ ማህበራት የተውጣጡ የሰልፉ መሪዎች ወደ ቤተመንግስት የሚወስዱ መንገዶች እንዲዘጉ ለሰልፈኞቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰልፉ መሪዎች ሰልፈኞቹ ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት የሚወስዱትን መንገዶች ሁሉ እንዲዘጉ እና ሰልፈኞቹ በአካባቢው እንዲሰበሰቡ ጥሪ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
ሱዳናውያን ዛሬ በዋና ከተማቸው ዛሬ ለተቃውሞ የተሰበሰቡት ባለፈው የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት በመቃመም ሲሆን አሁን ሀገራቸውን የሚመራው መንግስት እንዲቀየርም ጭምር ነው።
በፈረንጆቹ ጥቅምት 25 በተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተነስተው የነበሩት የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በድጋሚ ወደ ሃላፊነት በመምጣታቸው እና ከአልቡርሃን ጋር ስምምነት መፈራረናቸው እንደሆነም ተገልጿል።
በሰልፉ በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ ግልጽ ባይደረግም ከፍተኛ የሆነ የሰው ቁጥር እንደተሳተፈበት ተገልጿል። የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸውንም መቀመጫቸውን ሱዳን ያደረጉ መገናኛ ብዙሃን እዘገቡ ናቸው።
የቀድሞው ሱዳን መሪ ኦማር ሃሰን አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ ምክንያት የሆነው ህዝባዊ ተቃውሞ የተቀጣጠለበት ሶስተኛ ዓመቱ ነው።