በቻይና የደረሰ ርዕደ መሬት ከ118 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ
በርዕደ መሬት መለኪያ 6 ነጥብ 2 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ ከ5 ሺህ በላይ ቤቶችን ማፈራረሱም ተገልጿል
በምዕራባዊ ቻይና በ2008 የደረሰ ርዕደ መሬት 70 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት መቀማቱ ይታወሳል
በሰሜን ምዕራብ በደረሰ የርዕደ መሬት አደጋ በጥቂቱ የ118 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
ጋንሱ እና ሺንሃይ በተባሉት ግዛቶች የደረሰው አደጋ በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 2 ሆኖ ተመዝግቧል።
ከ400 በላይ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገው የርዕደ መሬት እኩለ ሌሊት ላይ መከሰቱን ሽንዋ ዘግቧል።
አደጋው ከ5 ሺህ በላይ ቤቶችን ማፈራረሱንና የነፍስ አድን ስራውም ተጠናክሮ ስለመቀጠሉም ነው እየተነገረ ያለው።
በአካባቢው ያለው የሙቀት መጠን ከዜሮ በታች 13 ዲግሪ ሴልሺየስ መሆኑ የነፍስ አድን ስራውን ክፉኛ ማወኩንም ነው ሲሲቲቪ የዘገበው።
ከ3 ሺህ በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን በግዛቶቹ ያሰማራችው ቤጂንግ ፥ ለአስቸኳይ የአደጋ ምላሽ ስራዎች 28 ሚሊየን ዶላር መድባለች ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግም አስቸኳይና ሁሉን አቀፍ የነፍስ አድን ዘመቻ እንዲጀመር ማዘዛቸው ተገልጿል።
ቻይና የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትላት ታይዋን በአደጋው ሀዘኗን በመግለጽ ለቤጂንግ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።
ምዕራባዊ ቻይና (ዛሬ አደጋ የደረሰባትን ጋንሱን ጨምሮ) በተደጋጋሚ የርዕደ መሬት የሚጎበኘው አካባቢ ነው።
በቻይና እስካሁን በአስከፊነቱ በቀዳሚነት የሚነሳው በፈረንጆቹ 2008 በሬክተር ስኬል 8 ነጥብ 0 ሆኖ የተመዘገበውና የሲቹዋን ግዛትን ያፈራረሰው ርዕደ መሬት ነው። በዚህ አደጋ 70 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ማለፉን ሬውተርስ አስታውሷል።