እቅዱ በስድስት ግዛቶች የሚገኙ 4.2 ሚሊዮን ሰዎችን ለማገዝ ያለመ ነው
በከባድ ርዕደ መሬት የተመታችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለምታደርገው መልሶ ግንባታ 11.7 ቢሊየን ዶላር ወጪ ለማድረግ አቅዳለች።
በሀገሪቱ ከሁለት ሳምንታት በፊት በደረሰው ርዕደ መሬት 3 ሺህ የሚደርሱ ሸዎች ህይወት አልፏል።
አደጋው በተለይም በአትላስ ተራራማ ቦታዎች ከመክፋቱ ባሻገር የአካባቢው ተደራሽነት የነፍስ አድን ጥረቶችን ፈታኝ አድርጓል።
እቅዱ በአደጋ ክፉኛ በተመቱ ስድስት ግዛቶች የሚገኙ 4.2 ሚሊዮን ሰዎችን ለማገዝና መልሶ ለማቋቋም ያለመ ነው ተብሏል።
የሞሮኮ ቤተ መንግስት ይፋ ያደረገው እቅድ የቤቶችና የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን ያካተተ ነው።
በርዕደ መሬት የተመቱት የሞሮኮ አካባቢዎች ድሃና የመሰረተ-ልማት ዝርጋታዎች ያልደረሰባቸው ናቸውም ተብሏል።
ቤተ መንግስቱ ባወጣው መግለጫ ገንዘቡ ከመንግስት፣ ከዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶችና ለአደጋው ሲባል ከተከፈቱ ፈንዶች ይሰባሰባል ብሏል።
ለርዕደ መሬቱ መቋቋሚያ እስካሁን 700 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።