ሩሲያ ርዕደ መሬት እና ጎርፍ የሚያስነሱ የጦር መሳሪያዎችን እየሰራች መሆኑ ተነገረ
መሳሪያዎቹ ከዚህ ቀደም በጦር አውድማ ያልተሞከሩና አዲስ አሰራርን የሚከተሉ ናቸው ተብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2023/9/14/273-131750-putin_16502cfbe6a169_700x400.jpg)
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸውን ከቀጣይ ስጋት ይታደጋሉ ያሏቸውን ዘመናዊ መሳሪያዎች አስተዋውቀዋል
ሩሲያ በጦርነት ቀጠና ርዕደ መሬት እና ጎርፍ በማስነሳት ለድል ያበቁኛል ያለቻቸውን አዳዲስ መሳሪያዎች እያመረተች መሆኑን አስታወቀች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በቭላዲቮስቶክ ከተማ በተካሄደ ጉባኤ እነዚህ መሳሪያዎች የሞስኮን ቀጣይ የደህንነት ስጋት የሚቀንሱ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
ፑቲን ስለአዳዲሶቹ መሳሪያዎች ፍንጭ ከመስጠት ውጭ ባያብራሩም ስፑትኒክን ጨምሮ የተለያዩ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን የመሳሪያዎቹን አይነትና አገልግሎት በተመለከተ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው።
አዳዲሶቹ መሳሪያዎች ከዚህ ቀደም በየትኛውም የጦር አውድማ ጥቅም ላይ ያልዋሉና አጠቃቀማቸውም የተለየ ስልት የሚጠይቅ መሆኑ ተነግሯል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደሚለው የእነዚህ የጦር መሳሪያዎች ውጤታማነት (የማውደም አቅም) የሚለካው በሂደቱ እና በጦርነቱ አካባቢ ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ነው።
እስካሁን በውጊያ ወቅት ጥቅም ላይ አልዋሉም የተባሉት መሳሪያዎች ቃታ በመሳብ የሚተኮሱ ሳይሆኑ በኤሌክትሮማግኔቲክ ሃይል ከርቀት የሚሰሩና ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትሉ ናቸው ብሏል ሚኒስቴሩ።
“ሌዘር”፣ “አክስለሬተር” እና “ማይክሮዌቭ” የሚሰኙት የመሳሪያ አይነቶች የጠላትን ወታደሮች፣ የጦር መሳሪያዎች እና መሰረተ ልማቶች ለማውደም ይውላሉ።
ሞስኮ የአስለቃሽ ጭስ፣ የጎማ ጥይት እና የመሳሰሉ የሀገር ቤት ተቃውሞዎችን ለመበተን የሚውሉ መሳሪያዎችን የሚተኩ አዳዲስ (“Non-lethal weapons”) መሳሪያዎችንም እያመረተች መሆኑ ተዘግቧል።
የብዙሃኑን ትኩረት የሳቡት ግን የተፈጥሮ ሃይልን ለወታደራዊ ጥቅም ያውላሉ የተባሉት “Geophysical weapons” ናቸው።
እነዚህ መሳሪያዎች ምድራችን ውስጥ ከሚገኙ ጠጣር፣ ፈሳሽ ወይም ጋዛማ ነገሮች ጋር በመዋሃድና በአየር ንብረት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ነውጥ መፍጠር የሚችሉ ናቸው ተብሏል።
መሳሪያዎቹ ከባድ ፍንዳታን በመፍጠር ርዕደ መሬት፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እና ጎርፍን ማስከተል ይችላሉ የተባለ ሲሆን የጠላት ቀጠና ነው የተባለ አካባቢን የአየር ሁኔታ እስከመቀየር ይደርሳሉኡ ይላል ስፑትኒክ በዘገባው።
ሩሲያ ከኒዩክሌር ዝቃጭ የሚሰሩና ከባቢ አየርን የሚመርዙ (“Radiological weapons”) መሳሪያዎችንም እየሰራች ስለመሆኑ ነው የተዘገበው። እነዚህ መሳሪያዎች ከቦምብ እና የሚሳኤል አረር ላይ ተሰክተው ሊተኮሱ የሚችሉ ናቸው። መሳሪያዎቹ ከተተኮሱ በኋላ ከባቢ አየርን እስከ 100 አመት ድረስ ሊበክሉ እንደሚችሉም ተጠቅሷል።
ሞስኮ ማረጋገጫ ባትሰጥበትም የሰው ልጆችን ዘረመል መሰረት በማድረግ የሚሰሩ ቫይረሶች እና አደገኛ ውህዶች (“genetic weapons”)ም እያመረተች ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም የባዮሎጂካል ጦር መሳሪያዎችን አደገኛነት ከመጥቀስ ውጭ ያለው ነገር የለም።