“ወጣት መሳዩዋ አዛውንት” በ60 አመቷ ለአርጀንቲና የቁንጅና ውድድር አልፋለች
በመዲናዋ ቦነስ አይረስ በተካሄደ የቁንጅና ውድድር ያሸነፈችው ጠበቃና ጋዜጠኛ፥ “ውበት በእድሜ አይገደብም” ብላለች
በሳምንት ለሶስት ቀናት ስፖርት መስራቷና አመጋገቧ ውበቷን ጠብቃ ለመቆየት እንዳስቻላትም ትናገራለች
በአርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስ በቅርቡ በተካሄደ የቁንጅና ውድድር የ60 አመቷ አሌጃንድራ ማሪሳ ሮድሪጌዝ አሸንፋለች።
ጠበቃና ጋዜጠኛዋ ሮድሪጌዝ፥ በግንቦት ወር መጨረሻ በሚካሄደው የአርጀንቲና ቆነጃጅት ውድድር ማለፏን አረጋግጣለች።
በ20ዎቹ አልያም በ30ዎቹ ውስጥ የምትገኝ ወጣት እንጂ የ60 አመት አዛውንት የማትመስለው ሮድሪጌዝ ወጣት ቆነጃጂቶችን ማሸነፏ በአርጀንቲና የማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ እንድትሆን አድርጓታል።
የአለም የቁንጅና ወድድር ከፈረንጆቹ 1958 ጀምሮ ሲካሄድ ተወዳዳሪዎች እድሜያቸው ከ18 እስከ 28 አመት ባለው እንዲሆን ገደብ ተቀምጦ ነበር።
ባለፈው አመት ግን የእድሜ ገደቡ መነሳቱ እንደ ሮድሪጌዝ ያሉ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ በሩን ከፍቷል።
“የ2024 የቦነስ አይረስ ቁንጅና ውድድርን በማሸንፌ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ለሁሉም ሴቶች ውበት እድሜ እንደሌለው እና መሰናክሎችን መበጣጠስ እንደሚቻል ማሳየት እፈልጋለሁ” ብላለች አሸናፊዋ።
እድሜዋ አሁንም አከራካሪ ሆኖ የቀጠለው ማሪሳ ሮድሪጌዝ፥ በሳምንት ለሶስት ቀናት ስፖርት መስራቷና በጊዜ የተገደበ አመጋገብ (አንድ ጊዜ ተመግቦ ለረጅም ስአት ከምግብ መራቅ) መከተሏ አቋምና የፊት ገጽታዋ የወጣት እንዲመስል እንዳደረገው ትገልጻለች።
ከባሏ ጋር ተፋታ ብቻዋን መኖሯም በቁንጅና ውድድሩ ስኬታማ እንድትሆን ሳያግዛት እንዳልቀረ በቀልድ መልክ ተናግራለች።
“ውበት የሚያበቃበት የጊዜ ገደብ የለውም፤ ወሳኙ ጉዳይ በራስ መተማመን እና ራስን ሆኖ መገኘት ነው” የምትለው የ60 አመቷ ሮድሪጌዝ፥ በውድድሩ ያሳየችው በራስ መተማመን ለውጤት እንዳበቃት ታምናለች።
ሮድሪጌዝ ግንቦት 25 2024 በሚደረገው የወይዘሪት አርጀንቲና ውድድር በማሸነፍ ሀገሯን በአለማቀፉ መድረክ ለመወከል ዝግጅት እያደረገች መሆኑን መግለጿንም ኦዲቲ ሴንትራል ነው ያስነበበው።