አለም የተጋረጠባትን የአየር ንብረት ቀውስ ለመቀነስ 650 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ
የበለጸጉት ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ ለሚገኙ ታዳጊ ሀገራት የሚያደርጉት ድጋፍ ግን ከሚጠበቅባቸው እጅግ ያነሰውን ነው
በፓሪስ በተካሄደው የአለማቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ለሚያግዙ ስራዎች የ100 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል ተገብቷል
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በህንድ በ60 አመት ውስጥ ከፍተኛው ሙቀት ተከስቷል።
በቺሊ፣ አሜሪካ፣ ቱርክና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በስፋት እየተከሰተ ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሚሊየኖችን ለረሃብ ያጋለጡ አደጋዎችም የተከሰቱት በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ተጋርጦባቸዋል የተባሉት 10 ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው ድርሻ ግን በጣም አነስተኛ ነው። አስሩም ሀገራት በድምሩ ያላቸው ድርሻ 0 ነጥብ 28 በመቶ ብቻ ነው።
ሀገራቱ ከገቡበት ችግር እንዲወጡ ዋነኞቹ በካይ ሀገራት ሊያደርጉት ስለሚገባው ድጋፍ ተደጋግሞ ቢነሳም የገቡትን ቃል ሲፈጽሙ አይታይም።
ለአረንጓዴ ልማት የሚቀርበው ብድርም አነስተኛ መሆንና ወለዱም አበረታች አለመሆኑ በእነዚህ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግር ውስጥ ለወደቁ ሀገራት ፈተና ሆኗል።
ባለፈው ሳምንት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የአለማቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባኤም ይሄው ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት ተደርጎበታል።
“ብሪጅታውን ኤኒሼቲቭ”
“ብሪጅታውን ኤኒሼቲቭ” በአለማችን ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙት (የበለጸጉ ሀገራት) በስተደቡብ ለሚገኙትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዘርፈ ብዙ ችግር ለተደቀነባቸው ታዳጊ ሀገራት ስለሚደረግ ድጋፍ ምክረ ሃብሳቦችን ያቀርባል።
በካሪቢያን ደሴቷ ሀገር ቤርባዶስ ዋና ከተማ የተሰየመው ኤኒሼቲቩ በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ ይመራል።
በፓሪሱ ጉባኤም አለማቀፍ አበዳሪ ተቋማት ለታዳጊ ሀገራት የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ድጋፍ እንዲሰጡ የሚወተውተው የብሪጅታውን ኤኒሼቲቭ ተግባራዊ እንዲደረግ ተጠይቋል ይላል ፋይናንሽያል ታይምስ።
በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ለተጎዱ ሀገራት የ650 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያስፈጋል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞትሌይ፥ እንደ አለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ያሉ አበዳሪ ተቋማት ለሀገራቱ አዲስ የድጋፍ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል።
በፓሪሱ ጉባኤ የአለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ለሚውሉ ስራዎች የ100 ቢሊየን ዶላር ብድር በአነስተኛ ወለድ ለማቅረብ መስማማቱን ገልጿል።
የብሪጅታውን ኤኒሼቲቭ ግን አለም ከተደቀነባት ፈተና አንጻር ከዚህም በላይ ትብብርና ድጋፍ ያሻል ብሏል።
በሰባቱ የበለጸጉ ሀገራት ከሚመሩት የአለማቀፍ አበዳሪ ተቋማት እና የዶላር ጥገኝነት መላቀቅ እንደሚገባም በፓሪሱ ጉባኤ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ቻይና ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በፈረንጆቹ 2014 ያቋቋመችው የ”ኒው ዴቨሎፕመንታል ባንክ” በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በገጠመው ችግር ለሞስኮ ጭምር ብድር ማቅረብ አልቻለም።
ሌላኛው ቻይናን ጨምሮ ከ100 በላይ ሀብታም መንግስታት ንብረት የሆነው የእስያ ኢንቨስትመንት ባንክም የአለም ባንክ እና አይኤምኤፍን ደጅ ጥናት ሊያስቀር አልቻለም።
የአለም የፋይናንስ ስርአት ካልተስተካከለና የበለጸጉት ሀገራት አለምን እየበከሉ የድጋፍ እጃቸውን ከሰበሰቡ ምድራችን ከእስካሁኑ የከፋ የአየር ንብረት ለውጥን ማስተናገዷ አይቀሬ ይመስላል።