የአኩሪ አተር ምርታማነትን ለማሳደግ ጥቅም ላይ የዋለው ድሮን
በአሜሪካ ኢንዲያና ግዛት ተመራማሪዎች የአኩሪ አተር እድገትን በድሮን በመከታተል ላይ ናቸው
በድሮን የሚነሱት ምስሎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአኩሪ አተር ዝርያን ለመለየት ያግዛሉ ተብሏል
በሰሜን እና ማዕከላዊ አሜሪካ የሚገኙ አርሶ አደሮች አኩሪ አተር በብዛት ያመርታሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት ግን የአኩሪ አተር ምርታማነት በየአመቱ እየቀነሰ መሄዱ ይነገራል።
በኢንዲያና ግዛት የሚገኘው ፐርድዩ ዩኒቨርሲቲም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአኩሪ አተር ዝርያን ለመለየት ምርምር ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።
በቅርቡም ድሮኖችን ጥቅም ላይ አውሎ ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን ሞርኒንግ ኢን ክሊፕስ የተሰኘው ድረገጽ አስነብቧል።
ኬቲ ሬኔይ እና ኬት ቺርከር የተባሉት ተመራማሪዎች በማሳ ላይ የሚገኝ አኩሪ አተር እድገትን በተለያየ አቅጣጫ ምስል የሚያነሱ ድሮኖችን ወደ ስራ አስገብተዋል።
ድሮኖቹ በየቀኑ የሚያነሱት ምስል የተዘራው አኩሪ አተር የእድገት ደረጃ እና የባዮማስ መጠን ለመለየት እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።
በፐርድዩ ዩኒቨርሲቲ የአኩሪ አተር ምርምር ማዕከል ሃላፊዋ ኬቲ ሬኔይ፥ በድሮኖቹ የሚነሱት ምስሎች በማዕከሉ መሳሪያዎች ሲተነተኑ የተገኘው ውጤት አስደሳች ነው ብለዋል።
በቀጣይም ተለዋዋጭ በሆነ የአየር ንብረት ሁኔታ ቢዘራ ፍሬያማ ፍሬ ያለውን የአኩሪ አተር ዝርያ ለመለየት ለምናደርገው ምርምር የድሮኖቹ በጣም በቅርበት የሚነሱት ምስሎች እጅግ አጋዥ እንደሚሆኑም ነው ያብራሩት።
በአሜሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአኩሪ አተር ዝርያን ለማግኘት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።
በዘርፉ የተለየ የምርምር ውጤት ይዘው ለሚመጡ ተመራማሪዎችም እስከ 900 ሺህ ዶላር ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት አቋቁመዋል።