በ30 አመት ውስጥ ዘግናኝ ነው በተባለ አውሮፕላን አደጋ የ68 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ
68 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ነው ፖክሃራ በተባለ አካባቢ የተከሰከሰው
ከአደጋው የተወሰኑ ሰዎችንም ቢሆን ህይወት ለማትረፍ ጥረቱ ቀጥሏል
በኔፖል በ30 አመት ውስጥ ዘግናኝ በተባለ የአውሮኘላን የመከስከስ አደጋ ቢያንስ 68 መሞታቸውን የአቬሽን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ 68 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር ተብሏል።
በኔፓል ከአምስት አመት ወዲህ በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈበት አደጋ የተከሰተው ዛሬ ጠዋት ፖክሃራ በተባለ አካባቢ ነው።
የ68 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢውን ባለስልጣናት የጠቀሱ የኔፓል መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም የነፍስ አድን ሩጫ ላይ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
አውሮፕላኑ በእሳት መያያዙና በተራራማ ስፍራ መከስከሱ የነፍስ አድን ስራውን ማወኩ ተነግሯል።
የየቲ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን አራት የበረራ ቡድንን አባላት እና 68 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ነበር ተብሏል።
ከተጓዦቹ መካከልም አምስት ህንዳውን፣ አራት ሩሲያውያን፣ ሁለት የደቡብ ኮሪያ እና የአውስትራሊያ ዜጎች እንደሚገኙበት ነው የተነገረው።
የኔፓል የአቬይሽን ባለስልጣን የአደጋውን መንስኤ ባይገልጽም፥ አውሮፕላኑ ከካታማንዱ ሲነሳ ደመና እንዳልነበር አስታውቋል።
ግማሹ የአውሮፕላኑ ክፍል በተራራ ላይ ተንጠልጥሎ የቀረ ሲሆን ቀሪው ክፍል ሰቲ ወደተባለ ባህር መግባቱም እየተዘገበ ነው።
የዛሬው አደጋ በመጋቢት ወር 2018 ከደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ወዲህ በርካቶችን ለህልፈት የዳረገ ነው ተብሏል።
በወቅቱ ከዳካ ተነስቶ ካታማንዱ ለማረፍ ሲሞክር የነበረ አውሮፕላን የመገልበጥ አደጋ ደርሶበት የ51 ሰዎች ህይወት ማለፉን ሬውተርስ አስታውሷል።
ከአለማችን 14 ረጅም ተራራዎች ስምንቱ የሚገኝባት ኔፓል የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ይደጋግማታል።
ጭጋጋማ የአየር ንብረቷም ለአውሮፕላን ጉዞ ፈታኝ በመሆኑ የአውሮፓ ህብረት በፈረንጆቹ 2013 የኔፓል አየርመንገድ አውሮፕላኖችን ከበረራ ቀጠናው ማገዱ የሚታወስ ነው።