የቅጣት ውሳኔው የተጣደፈ እና በዝግ በተካሄዱ ችሎቶች የተላለፈ ነው በሚል ተቃውሞዎች ቢበረከቱም ቴህራን አመጹን ለማስቆም የስቅላት እርምጃውን ገፍታበታለች
ኢራን ለአመጽ አደባባይ በመውጣት አንድ በጎፈቃደኛ ወታደርን ገድለዋል ያለቻቸውን ሁለት ግለሰቦች በስቅላት ቀጣች።
ሞሃመድ ሜህዲ ካራሚ እና ሞሃመድ ሁሴን የተባሉት ግለሰቦች ናቸው በትናንትናው እለት በስቅላት የተቀጡት።
ሩሆላህ አጃሚን የተባለውን ወታደር በካራጂ ከተማ ገድለዋል የተባሉት ተከሳሾች ጥፋታቸውን ማመናቸውና አገዳደሉንም ማሳየታቸውን የጠቀሰው የኢራን አብዮታዊ ፍርድ ቤት በቴሌቪዥን ብዙ አርትኦት የተሰራበት የቪዲዮ ምስል ለቋል ተብሏል።
የክስ ሂደቱ እጅግ ተጣድፏል፤ ችሎቶቹም በዝግ የተካሄዱ ናቸው ያሉ የመብት ተሟጋቾች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል “የችሎት ሂደቱ ምንም አይነት ህጋዊ አካሄድ የተከተለ አይደለም” የሚል መግለጫውን አውጥቷል።
የኢራን የመብት ተሟጋቾችም እስካሁን 16 ሰዎች በተቃውሞው ምክንያት በዝግ ችሎት የሞት ቅጣት ሳይፈረድባቸው እንዳልቀረ እየገለጹ ነው።
የማሻ አሚኒ ግድያን ተከትሎ ከመስከረም ወር ወዲህ በተቃውሞ ውስጥ ያለችው ቴህራን ትናንት አራተኛውን የስቅላት ቅጣት ነው የፈጸመችው።
ከመስከረም ወር ጀምሮ ከ517 በላይ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ኢራናውያን መገደላቸውና ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
የኢራን ባለስልጣናት ግን ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉና እንደተያዙ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በትናንትናው እለት አዲስ የፖሊስ አዛዥ መሾማቸውም ተቃውሞውን ለማፈን የተያዘው እቅድ ማሳያ ነው እየተባለ ነው።በፈረንጆቹ ከ2008 እስከ 2014 የፖሊስ አዛዥ ሆነው ያገለገሉት ጄኔራል አህመድ ረዛ ራዳን ናቸው ዳግም ስልጣን የተሰጣቸው።
በ2009 የድህረ ምርጫ ተቃውሞችን ለማስቆም በወሰዱት ጭካኔ የተሞላበት ውሳኔ የሚታወቁት ራዳን፥ በአሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ማዕቀብ ተጥሎባቸው መቆየቱ ይታወሳል።በአሁኑ ወቅትም የኢራናውያን ተቃውሞ ለማብረድ ራዳን ሁነኛ ሰው ናቸው ተብለው ተሹመዋል ነው የተባለው።