በሩሲያ ጥቃት የተደናገጡት ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ያስፈልገናል ሲሉ ምዕራባውያንን ተማጸኑ
ሩሲያ የዩክሬኗን የማዕድን ከተማ ሶሌዳርን መያዟን የኪቭ ባለስልጣናትን ያስደነገጠ ይመስላል
ዘሌንስኪ ፤ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ማቆም የሚቻለው አጋሮች አስፈላጊ መሳሪያዎችን ካቀረቡ ብቻ ነው ብለዋል
በሩሲያ ጥቃት የተደናገጡት ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ያስፈልገናል ሲሉ ምዕራባውያንን ተማጽነዋል፡፡
ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ቅዳሜ እንደተናገሩት የሩሲያ ጦር በሲቪል ኢላማዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም የሚቻለው የዩክሬን አጋሮች አስፈላጊ መሳሪያዎችን ካቀረቡ ብቻ ነውም ብለዋል፡፡
" አሁን በዩክሬን ምድር እየሆነ ያለው አሳዛኝ ነገር ለማስቆም ምን ያስፈልጋል? በማለት ጥያቄ የሚያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ መልሱ የምዕራባውያን የተጠናከረ ድጋፍ መሆኑ መናገራቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
“እነዚያ በአጋሮቻችን መጋዘኖች ውስጥ ያሉት የጦር መሳሪያዎች" በድጋፍ መልክ ሊሰጡን ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል ዘሌንስኪ ፤ በዩክሬን ከተሞች ላይ ከዘነበው የሩስያ ሚሳኤል ጥቃት በኋላ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፡፡
ፕሬዝዳንቱ ስሜት በተቀላቀለበት ንግግራቸው "ሞትን የሚዘሩትን ምን እና እንዴት ማቆም እንዳለበት ዓለም ሁሉ ያውቃል፤ በዚህ ውስጥ የሚረዳንን ሁሉ አመሰግናለሁ" ሲሉም አክለዋል፡፡
ለቀናት የተካሄደውን ከባድ ጦርነት ተክተሎ የሩሲያ ጦር የማዕድን ከተማ ሶሌዳር መቆጣጠሩ ትልቅ ስኬት መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
የከተማዋን በሩሲያ ጦር መያዝ ለመቀበል ያቅማሙት ዩክሬን እና ምዕራባውያን በበኩላቸው የከተማዋን በሩሲያ ጦር እጅ መውደቅ የጦርነቱን አቅጣጫ እንደማይለውጥ በመናገር ላይ ናቸው፡፡
የሩሲያ የመከላከያ ሚንስቴር ሶሌዳር የተያዘችው የሩሲያ ጦር በሚሳይልና በመድፍ መሳሪያዎችን በመታገዝ በጠላት ላይ በሰነዘረው መጠነ ሰፊ ጥቃት መሆኑ ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ የከተማዋ መያዝ ያለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ሲለገልጽም ፤ ሶሌዳር በአቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ባክሙት ከተማ የሚወስዱትን መንገዶች ለመቁረጥ እና የቀሩትን የዩክሬይን ኃይሎች ለማጥመድ ያስችላል ብሏል።