የ6ኛው ዙር ሀገራዊ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በመካሄድ ላይ ይገኛል
ምርጫው በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እየተካሄደ ነው
12 የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው እየተሳተፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል
የ6ኛው ዙር ሀገራዊ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በዛሬው ዕለት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በ6ኛው ዙር ሀገራዊ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
ዛሬ እየተካሄደ ባለው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይም 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ መሆኑን ከምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እየተካሄደ መሆኑንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው።
ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ በአፋር ክልል የሲሆን፤ በክልሉ 4 ዞኖች፣ በ9 የምርጫ ክልሎች እና በ388 የምርጫ ጣቢያዎች እየተካሄደ ነው።
ገዢው ፓርቲን ጨምሮ 4 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፎካከሩበት በዚህ ምርጫ ላይ ከ550 ሺህ በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ በምርጫ ቦርድ የክልሉ ምርጫ ማስተባበሪያ አስታውቋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ቀሪና ድጋሚ ምርጫው በ3 ዞኖች እየተካሄደ ሲሆን፤ በአሶሳ ዞን በአሶሳ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመገኘት እየመረጡ ነው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 40 የምርጫ ጣቢያዎች የፀጥታ ችግር በመኖሩ በዛሬው ዕለት ድምፅ እንደማይሰጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ አስታውቋል
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስቃን ወረዳ እና ማረቆ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎችም ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በድምጽ መስጫ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፃቸውን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ፤ የፀጥታ ችግሮች ባለመስተካከላቸው አሁንም ምርጫ የማይደረግባቸው አካባቢዎች መኖራቸውም ተነስቷል።
አስቻይ ሁኔታዎች ሲኖሩ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተቀሩ ቦታዎች ምርጫ ለማካሔድ ቦርዱ ይሰራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በሁለት ዙሮች ሀገራዊ ምርጫ ያካሄደ ሲሆን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት የጸጥታ እና የተዓማኒነት ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ድጋሚና ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ይታወሳል።