ልዩልዩ
በጫሞ ሀይቅ ከሰጠመችው ጀልባ የሰባት ሰዎች አስከሬን ተገኘ
በአደጋው ህይወታቸው ካለፈ ስምንት ሰዎች እስካሁን ያልተገኘው የጀልባዋ ቀዛፊ አስከሬን ብቻ ነው
በሰባት ጀልባዎችና ዋናተኞች አስከሬን ፍለጋው ሲካሄድ ሰንብቷል
ቅዳሜ መጋቢት 16፤ 2015 ዓ.ም. በጫሞ ሀይቅ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል የሰባቱ አስከሬን ተገኝቷል።
በደቡብ ክልል ከአማሮ ልዩ ወረዳ ወደ አርባ ምንጭ ስምንት ሰዎችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ መስጠሟን ተከትሎ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
የአማሮ ልዩ ወረዳ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኃላፊ ሚልኪያስ ደቦጭ እስከ ትናንት ማታ ድረስ በተደረገ ፍለጋ የሰባት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ለአል ዐይን አረጋግጠዋል።
ኃላፊው የሁለት ሴትና የአምስት ወንድ አስከሬን ተገኝቷል ብለዋል።
የጀልባዋ ቀዛፊ(ሹፌር) አስከሬን ብቻ እንደሚቀር የተናገሩት ኃላፊው፤ በጀልባዎችና በዋናተኞች ፍለጋው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
"ማዕበልና ከፍተኛ ዝናብ" ለጀልባዋ መስጠም መንስኤ መሆኑን ሚልኪያስ ደቦጭ ቀደም ብለው ለአል ዐይን ተናግረዋል።
በሰባት ጀልባዎችና ዋናተኞች አስከሬን ፍለጋው ሲካሄድ ሰንብቷል።