ጀልባዋ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓም ሌሊት 13 የሚደርሱ ሰዎችና ድንች ጭና ጉዞ መጀመሯ ተነገሯል
በማእከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በጣና ሀይቅ ላይ በመጓዝ ላይ እንዳለች በተሰወረችው አነስተኛ ጀልባ ህይወቱ ያለፈ ካፒቴን አስከሬን መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።
በተሰወረችው ጀልባ ላይ ከነበሩት 13 ሰዎች አስከሬናቸው የተገኘ ሰዎች ቁጥር ስምንት መድረሱንም ኢዜአ ዘግቧል።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀይቁ በተሰወረችው ጀልባ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ለማግኘት በተደረገ የሶስተኛ ቀን ፍለጋ የካፒቴኑ አስከሬን ዛሬ ማለዳ በሃይቁ ማእበል ተገፍቶ ተንሳፎ ተገኝቷል።
በትናንትናው እለት የሰባት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን አስታውሰው፤ አጠቃላይ በጀልባዋ ህይወታቸው ያለፈና አስከሬናቸው የተገኘ ሰዎች ቁጥር ስምንት መድረሱን ተናግረዋል።
የቀሪዎቹን አምስት ሰዎች አስከሬን በአነስተኛ ጀልባዎችና በጠላቂ ዋናተኞች በመታገዝ የማፈላለግ ስራ እንደቀጠለ መሆኑንም አመልክተዋል።
በትናንትናው እለት የተገኘው የሰባት ሰዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቶ የቀብር ስነ-ስርአታቸው መፈጸሙንም ገልጸዋል።
ጀልባዋ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ለሊት ድንች የጫኑ 13 ሰዎችን አሳፍራ በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ መነሻዋን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ በጉዞ ላይ እንዳለች መሰወሯ ይታወሳል።
የጀልባዋ መነሻና መድረሻ የሀይቅ ላይ ጉዞ የ15 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዳለው ተነግሯል።