በኢትዮጵያ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ
በኢትዮጵያ እስከ ሰኔ 2012 ባለው ጊዜ 7 ሚሊዮን ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ብሔራዊ የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የድጋፍ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎችን በጥናት መለየቱንም አስታውቋል። በጥናቱ መሰረትም ለሰብዓዊ ድጋፉ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በሀገሪቱ ከቀደመው ጊዜ በተለየ የድርቅ ክስተት እየተደጋገመ በመምጣቱ የህዝቡን አኗኗርና የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እየጎዳ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በምግብ ፍላጎት ተረጂ የሆኑት 6 ሚሊዮን ሰዎች እንደሆኑና ባለፈው ዓመት ከነበረው 8 ሚሊዮን ተረጂዎች ጋር ሲነጻጻር ቁጥሩ መቀነስ ማሳየቱንም ተናግረዋል።
የዚህ ምክንያት ደግሞ በመኽር ምርት የተሸፈኑ የሰብል አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች በምርት ግኝት ማገገም በመቻላቸው ነው ተብሏል።
መንግስት ጉዳቱን ለመከላከልና ለመቋቋምም ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበርና ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለችግሩ ወቅታዊ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር አደጋውን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ ዘላቂ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ምንጭ ኢዜአ