የባህርዳር እና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች ማስተማር ጀመሩ
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በ21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም አስታውቋል
የባህርዳር እና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች መማር ማስተማር መጀመራቸውን አስታውቀዋል
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በአንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት ሆን ብለው በማወክ የተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ነው የገለጸው፡፡
እንደዩኒቨርስቲው የኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ከሆነ ሙሉ በሙሉ የታገዱ አራት ተማሪዎችን ጨምሮ ትምህርት እንዲስተጓጎል ያደረጉ 21 ተማሪዎች ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድም ዶ/ር ዘውዱ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ዜና የወለጋ ዩኒቨርሲቲም ከአንድ ወር በላይ አቋርጦት የነበረውን የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንትና ተማሪዎች ገለጹ በሚል ኢ.ዜ.አ እንደዘገበው ከሆነ ዩኒቨርስቲው ከጥር 12ቀን 2012 ጀምሮ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ጀምሯል፡፡
የባከነውን የትምህርት ጊዜ በሣምንቱ መጨረሻና በማታ መርሐ ግብር ለማካካስ ከመምህራንና ተማሪዎች ስምምነት መደረሱንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት የነበረው የቤተ መጽሃፍት አገልግሎት 24 ሰዓት ይሆናልም ተብሏል፡፡