በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን ለመደገፍ 658 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ 735,000 በላይ የውጭ ስደተኞች እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ባጠቃላይ የ26 ሀገራትን ስደተኞች የምታስተናግድ ሲሆን ከነዚህም አብዛኛው ከጎረቤት ሀገራት የመጡ ናቸው፡፡
የውጭ ስደተኞችን ጨምሮ ሀገሩስጥ ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ነው ለአውሮፓውያኑ 2020 ዓ.ም 658 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል የተባለው፡፡
ለዚህም ኮሚሽኑን ጨምሮ 57 የሰብአዊ ድርጅቶችን ያካተተ የኢትዮጵያ ስደተኞች ምላሽ መርሀ-ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል፡፡ መርሀ-ግብሩ በጤናና ስን-ምግብ፣ በትምህርትና መጠለያ እንዲሁም በንጽህና፣ የሀይል አቅርቦት እና መሰል ስደተኞች በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ይሰራል ነው የተባለው፡፡
ባለፈው ዓመት ወርሀ ጥር ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚገኙ ስደተኞች የስራ ፈቃድ፣ ትምህርትና የመንጃ ፈቃድ ማግኘት የሚችሉበትን ህግ ማዘጋጀቷን የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በበጎ ጎኑ ተመልክቶታል፡፡
ስደተኞች የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶችን እንዲያገኙና እንደ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማትን እንዲጠቀሙም አድርጋለች ይላል መግለጫው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችንም ስደተኞች እንደ አስፈላጊነቱ መጠቀም እንዲችሉ በቂ በጀት ያስፈልጋል ያለው ኮሚሽኑ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወነቻቸው ተግባርት የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
ስደተኞችን በማስተናገድ ረዥም ታሪክና ልምድ ያላት ኢትዮጵያ አሁን ላይ በጉያዋ ከምታስተናግዳቸው ከ730 ሺ በላይ ስደተኞች መካከል አብዛኛው በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህም ደቡብ ሱዳን(329,123)፣ ሶማሊያ(191,575)፣ ኤርትራ(139,281) እና ሱዳን (42,285) ሲሆኑ የተቀሩት የሌሎች 22 ሀገራት ዜጎች ናቸው፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 100 ሺ ያክል ስደተኞችን ስተናገደችው ኢትዮጵያ የምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር በየጊዜው በመጨመር ላይ ነው ኮሚሽኑ በመግለጫው እንዳስታወቀው፡፡