በታንዛኒያ የኤሊ ስጋ የተመገቡ 7 ዜጎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ
በኢንዶኔዥያ እና በህንድ በተመሳሳይ የኤሊ ስጋ የተመገቡ ሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል
የኤሊ ስጋ ከበሉት ውስጥ ሌሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ አሁንም በሆስፒታል ህክምና ላይ ናቸው ተብሏል
በታንዛኒያ የኤሊ ስጋ የተመገቡ 7 ዜጎች ህይወታቸው ማለፉ ተዘገበ፡፡
በምስራቃ አፍሪካዊቷ ሀገር ታንዛኒያ ዛንዚባር የኤሊ ስጋ የተመገቡ ሰባት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሶስት ሰዎች ደግሞ አሁንም በሆስፒታል እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
በዛንዚባር ፔምባ ደሴት የኤሊ ስጋ መመገብ የተለመደ ሲሆን የኤሊ ስጋ ከበሉት 10 ሰዎች ውስጥ የሶስት ዓመት ህጻንንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ይሁንና የታንዛኒያ መንግስት ዜጎች የኤሊን ስጋ እንዳይበሉ ያገደ ሲሆን ባሳለፍነው አርብ የኤሊ ስጋ በልተው በተጎዱ ሰዎች ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከሰዎቹ መሞት ጋር በተያያዘ 38 ሰዎች በሆስፒታል ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ሶስቱ ሰዎች ግን አሁንም በክትትል ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የታንዛኒያ ኤሊ ፋውንዴሽን በበኩሉ በፔምባ ደሴት የተመገቡት የኤሊ ስጋ ሊመረዝ እንደሚችል ገልጾ ህጻናት እና አዛውንቶች የበለጠ እንደሚጎዱ አስታውቋል፡፡ባሳለፍነው መጋቢት በማዳጋስካር የኤሊ ስጋ የተመገቡ 19 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ያታወሳል፡፡
በተጨማሪም በኢንዶኔዥያ እና በህንድ በተመሳሳይ የኤሊ ስጋ የተመገቡ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡