የኤርትራው አሊ ሱለይማን የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ጨርሷል
በኢትዮጵያ በባህርዳር ሲካሄድ የቆየው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች እግር ኳስ ውድድር በታንዛኒያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲያም ሲካሄድ የቆየው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ከ23 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።በዚህ ውድድር ላይ ታንዛኒያ ከብሩንዱ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ዛሬ ያካሄዱ ሲሆን ታንዛኒያ ዋንጫውን በልታለች።
ይህ የፍጻሜ ጨዋታ በሙሉ 90 ደቂቃ ያለምንም ጎል ተጠናቆ በመለያ ምት ታንዛኒያ 6 ለ5 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ቡድን አምበል አቡበከር ናስር የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ሲመረጥ የኤርትራው የፊት መስመር አጥቂ አሊ ሱለይማን የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ተመርጧል ።
የቡሩንዲ ግብ ጠባቂ ሩኩንዶ ኦንሲሜ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመባል መመረጡን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በዚህ ውድድር ላይ የደቡብ ሱዳን እግር ኳስ ቡድን ሶስተኛ ኬንያ 4ኛ ኤርትራ 5ኛ ኢትዮጵያ 6ኛ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ 7ኛ በመሆን አጠናቀዋል።