የዳሬሰላም፣ የሙዋንዛ እና የአዲሷ ዋና ከተማ ዶዶማ ነዋሪዎች የማጉፉሊን አስክሬን ሲሰናበቱ ነበር
”በልብ ህመም ምክንያት” ከዚህ ዓለም የተለዩት የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ የቀብር ሥነ ስርዓት ዛሬ በትውልድ ስፍራቸው ተፈጽሟል፡፡ የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ የቀብር ስነ ስርዓቱ ዛሬ ይካሄዳል ባለው መሰረት በቻቶ ተካሂዷል፡፡ አዲሷን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካታ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
የቀብር ስነስርዓቱ ትናንትና እንደሚካሄድ ቀደም ሲል ተገልጾ የነበረ ቢሆንም የሀገሪቱ ሕዝብ አስክሬን መሰናበት እንዲችል በሚል መርሃ ግብሩ ወደዛሬ መቀየሩ ይታወሳል፡፡ የዳሬሰላም፣ የሙዋንዛ እና የአዲሷ ዋና ከተማ ዶዶማ ነዋሪዎች ከሰሞኑ የጆን ማጉፉሊን አስክሬን ሲሰናበቱ ነበር፡፡
የ61 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ በቀድሞዋ የታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም በሚገኝ ሆስፒታል ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡ የጆን ማጉፉሊን ህልፈት ይፋ ያደረጉት የመጀመሪያዋ የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ሳሚያ ሱሉሁ ናቸው፡፡ የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት የጆን ማጉፉሊን ህልፈት ይፋ ከማድረጋቸው ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ከሕዝብ እይታ መሰወራቸውን ተከትሎ ሕዝቡ ተረጋግቶ ስራውን እንዲሰራ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
የጆን ማጉፉሊ የህልፈት ምክንያት ከልብ ህመም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይፋ ቢደረግም፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን ብዙ ትኩረት ሳይሰጡት ቀርተዋል የተባለው የኮሮና ቫይረስ ነው የሚሉ ሰዎች ግን አሉ፡፡ አዲሷ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን የቀድሞ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ህልፈት ተከትሎ የ14 ቀናት ብሔራዊ ሀዘን እንደሚታወጅ እና በዚህ ጊዜ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብም መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝደንት ማጉፉሊ ከሁለት ሳምንታት በላይ ለህዝብ አለመታየታቸውን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ ስለመታመማቸው ጭምጭምታዎች በሰፊው ሲናፈሱ ነበር።