ስልካችን በቫይረስ መጠቃቱን የሚያሳዩ ምልክቶች
የስልክ መሞቅና መንቀራፈፍ፣ የባትሪ በፍጥነት ማለቅ እንዲሁም የማናውቃቸው አዳዲስ መተግበሪያዎችና ማስታወቂያዎች መብዛት ስልካችን በቫይረስ መጠቃቱን ያመለክታሉ
ተአማኒ የጸረ ቫይረስ ሶፍትዌሮችን መጫንና ራሳችን ያልጫናቸውን መተግበሪያዎች ማስወገድ እንዲሁም የይለፍ ቃላትን ማጠንከር ከመፍትሄዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ
ከእለት ተዕለት ህይወታችን ጋር በጥብቅ የተሳሰሩት የስማርት ስልኮቻችን በቫይረስ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
በተለይ የአንድሮይድ ስልኮች ለተለያዩ የመረጃ መንታፊዎች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ስለመሆኑ ይነገራል።
የስልክ ቫይረስ አይነቶች በአምስት ይመደባሉ።
1. ማልዌር - ከተጠቃሚዎቹ እውቅና ውጪ ስልኮችን የሚበረብሩና የግል መረጃዎችን የሚመነትፉ ፕሮግራሞች
2. አድዌር - ስንጫናቸው የግል መረጃዎቻችን መቆጣጠር የሚያስችሉ ማስታወቂያዎች
3. ራንሰምዌር - የግል መረጃዎችን መንትፈው ክፍያ የሚጠይቁ ፣ ካልከፈላችሁ ምስሎችን ጨምሮ የግል መረጃዎችን ይፋ እናደርጋለን የሚሉ
4. ስፓይዌር - የግል የጎግልም ይሁን ሌላ የፍለጋ ውጤቶችን ታሪክ የሚቆጣጠሩና የስልካችን ፍጥነት የሚገድቡ
5. ትሮጃን - በመተግበሪያዎች ውስጥ በስውር ተደብቆ የስልኮችን ፍጥነትና መረጃ የሚቆጣጠር
ስማርት ስልኮች እንደ ኮምፒውተሮች ሁሉ በተለያዩ መንገዶች ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ይሆናሉ።
ተአማኒ ካልሆነ ምንጭ መተግበሪያዎችን መጫን (ከአፕ እና ጎግል ስቶር ውጭ)፣ በኢሜሎች የሚላኩ መልዕክቶችን በዘፈቀደ በመክፈት፣ ደህንነታቸው ያልተረጋገጠ የህዝብ ዋይፋይ መጠቀምና ያልተለመዱ ማስታወቂያዎችን መክፈት ለአደጋ ያጋልጣሉ።
እነዚህ ሰባት ምልክቶችም ስልኮቻችን በቫይረስ መጠቃታቸውን ያመላክታሉ።
1. ከእኛ እውቅና ውጭ የተጫኑ መተግበሪያዎች እና የአዳዲስ ማስታወቂያዎች መበራከት
2. የስልክ ሙቀት ከተለመደው በላይ መጨመር
3. ወደጓደኞቻችን በኢሜልና በማህበራዊ ሚዲያዎች ማስፈንጠሪያዎችን የያዙ መልዕክቶች ሲላኩ
4. የስልክ ቀፎዎች ፍጥነት መንቀራፈፍ
5. ከባንክ አካውንታችን ያልተለመደና ከፍተኛ ወጪ ሲደረግ (ከእኛ እውቅና ውጪ የክሬዲት ካርዳችን የመረጃ መንታፊዎች ሊጠቀሙበት ስለሚችል)
6. ስልካችን የዳታ ፍጆታው ሲበዛ
7. የስልካችን ባትሪ በፍጥነት ሲያልቅ
መፍትሄዎቹ፦
- ከታማኝ ምንጮች የጸረ ቫይረስ መተግበሪያዎች ወይም ሶፍትዌሮችን በመጫን በስልኮቻችንን ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን መለየትና ማስወገድ፣
- የመተግበሪያዎች ዝርዝር (አፕ ላይብረሪ) ውስጥ በመግባት ሁሉም መተግበሪያዎች ራሳችን የጫናቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ፤ ከእኛ እውቅና ውጪ የተጫኑትንም ማስወገድ፣
- ለአደጋ የሚያጋልጡ መልዕክቶችን እና የፍለጋ ውጤቶችን በፍጥነት ማጥፋት፣
- አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ስልካችን ሙሉ በሙሉ ወደቀደመ ይዞታው መመለስ (ሪቡት ማድረግ)፣ መረጃዎቻችን እንዳይጠፉም ጎግል ክላውድ ላይ ማስቀመጥ፣
- የይለፍ ቃላት (ፓስወርድ) ማጠንከርና በተለያየ ጊዜ መቀየር፣
- መተግበሪያዎችን በተቻለ ፍጥነት አፕዴት ማድረግ፣
- መተግበሪያዎች ለሚጠይቁት ሁሉ ፍቃድ አለመስጠት፣
- ከተአማኝ ምንጮች ውጭ መተግበሪያዎች አለማውረድና የሚያጠራጥሩ መልዕክቶችን እንዲሁም ማስታወቂያዎችን አለመክፈትም የስልካችን የቫይረስ ተጋላጭነት ለመቀነስ ወሳኝ ድርሻ አላቸው ተብሏል።