በትግራይ ክልል ለግብርና ስራ ከሚውል መሬት ውስጥ 70 በመቶው ላይ የግብርና ስራ ተጀምሯል- የግብርና ሚኒስቴር
የትግራይ ክልል በዘንድሮው ክረምት በቂ እና ከበቂ በላይ ዝናብ ያገኛል- ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ
350 ገደማ ቱረያ የሳተላይት ስልኮች ጥያቄ ሲያቀርቡ ለነበሩ የተራድኦ ደርጅቶች ተከፋፍሏል- ቢለኔ ስዩም
በትግራይ ክልል ለግብርና ስራ ከሚውል መሬት ውስጥ 70 በመቶው ላይ የስራ እንቅስቃሴ መጀመሩን የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ሳኒ ረዲ አስታወቁ።
ሚኒስትር ደኤታው እና የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ክንፈ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት በትግራይ ክልል እየተደረገ ስላለው የግብርና ዝግጅት እና የዝናብ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ሳኒ ረዲ በክልሉ ከሚገኙ 61 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ በ46 ቱ የግብርና ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በክልሉ ከሚገኘውና ለግብርና ከሚውለው 950 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 75 በመቶው በ46ቱ ወረዳዎች እንደሚገኝ ያነሱት አቶ ሳኒ፤ ይህም የግብርና ስራዉን በስፋት ለማስጀመር እንዳስቻለ ገልጸዋል።
በክልሉ ከሚገኙ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አርሶ አደሮች ውስጥም 70 በመቶው የግብርና ስራ መጀመራቸውን አስታውቀው፤ እስከ ሰኔ እና ሀምሌ መጨረሻ ድረስ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ወደ ቀያቸው ስለሚመለሱ የአርሶ አደሮች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል አስታውቀዋል።
ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ተመድቦ 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን እና ከ322 ሺህ በላይ ወደ መቐለ መጋዘን መግባቱን አስታውቀዋል።
ከምርጥ ዘር ጋር በተያያዘም 120 ሺህ ኩንታል በላይ ግዢ መፈጸሙን እና ከ44 ሺህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር ወደ ወረዳዎች መከፋፈሉንም ገልተጸዋል።
በአጠቃላይ በዘንድሮ መኸር ወቅት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ነው አቶ ሳኒ ያስታወቁት።
የብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ሀይለማርያም በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ክረምት በትግራይ ክልል በቂ እና ከበቂ በላይ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሰክረተሪያት ቢለኔ ስዩም በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ከተረአዶ ድርጅት ሰራተኞች ከቪዛ ጋር በተያያዘ ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቀዋል።
በዚህም የተረአዶ ድርጅቶች ሰራተኞች የ3 ወር ቪዛ እንዲያገኙ መደረጉን እና ቪዛው የሚራዘምበት ሁኔታም አበሮ መመቻቸቱን ገልጸዋል።
ከግንኙነት መሳሪያዎች ጋር በተያያዘም 350 ገደማ ቱረያ የሳተላይት ስልኮች ጥያቄ ሲያቀርቡ ለነበሩ የተረአዶ ደርጅቶች መከፋፈሉንም አስታውቀዋል።
ወደ ሽሬ ከተማ ቀጥታ የአውሮፕላን በረራ በቀጣይ አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ያነሱት ቢለኔ ስዩም፤ ይህም የሰብአዊ ድጋፍ ስራውን ለማቀላጠፍ ይረዳል ብለዋል።
በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ላይ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የሀሰት መረጃዎች እተዘዋወረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የኬሚካል የጦር መሳሪያ በትግራይ ጥቅም ላይ ውሏል በሚል የሌላ ስፍራን ምስል ትግራይ ውስጥ እንደተፈጸመ አስመስሎ ሲቀርብ ተስተውሏል ብለዋል።