በትግራይ “ርሃብ አለ ለማለት የሚያስችሉ ሁኔታዎች” የሉም-የኢትዮጵያ መንግስት
ኮሚሽነር ምትኩ “ምንም ዓይነት የምግብ እጥረት የለብንም”ም ሲሉ ተናግረዋል
ኮሚሽኑ የ5.4 ቢሊዬን ብር ዋጋ ያለው የምግብ ድጋፍ ለትግራይ ክልል መደረጉን ገልጿል
በትግራይ ክልል “ርሃብ አለ ለማለት የሚያስችሉ ሁኔታዎች”አለመኖራቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሉ የምግብ አቅርቦት ችግር እንደሌለም ገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ በክልሉ ረሃብ አጋጥሟል በማለት ተመድና ሌሎች አካላት ያቀረቧቸውን ሪፖርቶች አስተባብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ “ርሃብ አለ” ለማለት ሁኔታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ሶስት መስፈርቶችን ማሟላት አለባቸው፤ መስፈርቶቹም የማይነጣጠሉ እና አብረው ሊያጋጥሙ የሚገቡ ናቸው ብለዋል፡፡
መስፈርቶቹም ከአንድ አካባቢ ነዋሪዎች በትንሹ 20 በመቶ ያህሉ ለከፋ የምግብ እጥረት ሲጋለጡና ለመቋቋም የሚችሉበትን አቅም ሲያጡ፣ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአካባቢው ህጻናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሲገጥማቸው እና ከ10ሺ ሰዎች መካከል ቢያንስ በየቀኑ ከ2 በላይ ሰዎች በርሃብ ምክንያት ሲሞቱ የሚሉ ናቸው፡፡
ሆኖም አሁን ላይ በክልሉ “ርሃብ አለ፤ ለከፋ የርሃብ አደጋ ሊጋለጥም ይችላል” በሚል የሚቀርቡ ሪፖርቶች የመጀመሪያውን መስፈርት ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚቀርቡ ናቸው እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ፡፡
በመስፈርቶቹ መሰረት ከአጋሮቻቸው ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ነው የገለጹት፡፡
አቶ ምትኩ “ምንም ዓይነት የምግብ እጥረት የለብንም”ም ነው የሚሉት፡፡
ከመንግስት በተጨማሪ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 91.3 በመቶ ያህሉን ለመድረስ የቻሉና በዩኤስ ኤይድ በሚደገፉ 5 አጋሮቻችን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረጉ ነው ሲሉ ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ከህግ ማስከበር ዘመቻው መጠናቀቅ ወዲህ በተለያዩ ዙሮች የተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡
የ5.4 ቢሊዬን ብር (135 ሚሊዬን ዶላር) ዋጋ ያለው 170 ሺ 798 ሜትሪክ ቶን ድጋፍ ምግብም ተሰራጭቷል፡፡
ከሶስት የድጋፍ ዙሮች መጠናቀቅ በኋላ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ 6 ድጋፍ አድራጊ አጋር ተቋማት በክልሉ ተሰማርተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 5ቱ በዩ ኤስ ኤይድ ይደገፋሉ የተባለላቸው አጋር ተቋማት ናቸው፡፡
ይህ መሆኑም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግና ከድጋፉ ፈላጊዎች 91.3 በመቶ ያህሉን ለመድረስ አስችሏል፡፡
ሆኖም አሉ ባሏቸው “አድፍጠው ምግብ በጫኑ ተሽከርካሪዎች እና በሰዎች ላይ የሚተኩሱ የህወሓት ርዝራዦች” ምክንያት ታች ያለውን ማህበረሰብ በሚታሰበው ልክ ለመድረስ መቸገራቸውን አልሸሸጉም፡፡
ይህን ለመቅረፍ ከመከላከያ እና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ከሰሞኑ በርካታ የትግራይ አካባቢዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ዋና ጸሃፊው የትግራይ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው ሲሉም ነበር ያሳሰቡት፡፡
የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ /ኦቻ/ም የጉዳዩን አሳሳቢነት በማስታወቅ ምናልባትም ከ1970ዎቹ ወዲህ ያልታየ ከፍተኛ የረሀብ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ገልጾ ነበር፡፡
በኦቻ የወጣውና በዝግ ለተሰበሰበው የጸጥታው ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት በኮረም ኦፍላ ወረዳ ያለውን ሁኔታ የሚያትት ነው ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ በወረዳው እንደተባለው ዓይነት ሁኔታ እንደሌለ እና በአካባቢው ሰብዓዊ ድጋፎችን ከማድረስ የሚያስተጓጉሉ መሰናክሎች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርቱ “ሆን ተብሎ በክልሉ በሚሰሩ አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቀረበ ውሸት መሆኑን ከአንዴም ሁለቴ አረጋግጠናል”ም ብለዋል፡፡
ከአጠቃላይ የክልሉ ህዝብ 90 በመቶ ያህሉ (5.2 ሚሊዬን ህዝብ) አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍን የሚሻ ነው በሚል የሚወጡ ሪፖርቶችም አሉ፡፡
ሆኖም ሪፖርቶቹ አስቸኳይ ድጋፍ የማያስፈልጋቸውንና ቀደም ሲል የተያዘ የራሳቸው ሃብት ያላቸውን በልማታዊ ሴፍቲ ኔት መርሐ ግብር የታቀፉ 1 ሚሊዬን 10 ሺ 752 ተጠቃሚዎችንና 40 ሺ 336 ኤርትራውያን ስደተኞችን ማካተታቸውን ኮሚሽነር ምትኩ ተናግረዋል፡፡