በትግራይ ክልል ያለው አሳዛኝ ሰብአዊ ቀውስ ከፍተኛ የድንገተኛ አደጋ ስጋት ላይ መድረሱ በእጅጉ ያሳስበኛል - ኢሰመኮ
መንግስት “በክልሉ ርሃብ አለ ለማለት የሚያስችሉ ሁኔታዎች የሉም” ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነው
በምግብ እጥረት የተጎዱ የሕፃናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋማት እንደደረሱትም ኮሚሽኑ አስታውቋል
በትግራይ ክልል ያለው አሳዛኝ ሰብአዊ ቀውስ ከፍተኛ የድንገተኛ አደጋ ስጋት ላይ መድረሱ በእጅጉ እንደሚያሳስበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኢሰመኮ የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (Integrated Food Security Phase Classification) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንደተጠቀሰው በትግራይ ክልል ያለው አሳዛኝ ሰብአዊ ቀውስ ከፍተኛ የድንገተኛ አደጋ ስጋት ላይ መድረሱ በእጅጉ ያሳስበኛል ብሏል፡፡
በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋማት ለኮሚሸኑ የደረሱት ሪፖርቶች በምግብ እጥረት የተጎዱ የሕፃናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ማመልከታቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽነት በአፋጣኝ የማረጋገጥን አስፈላጊነት ያነሳው ኮሚሽኑ ተደራሽ በሆኑ አብዛኛው አካባቢዎች ጭምር ያለውን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እጥረት ለሟሟላት ተገቢጥረት መደረግ እንዳለበት በአፅንዎት አሳስቧል፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ያደረጋቸውን ጥሪዎች ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ “ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መቆየት የማይችለው አስቸኳይ ጉዳይ ግን አስፈላጊውን አቅምና ሀብት ሁሉ በማሰባሰብ የሰብአዊ እርዳታን ተደራሸነት ማረጋገጥ እና ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች እርዳታ ማድረግ” እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በክልሉ ያለው ሁኔታ የከፋ ርሃብን ሊያስከትል እንደሚችል በማሳሰብ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ሲያስጠነቅቅ ነበር፡፡
የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (OCHA) በክልሉ 350 ሺ ገደማ ዜጎች ለርሃብ ተዳርገዋል ሲል መግለጫ ማውጣቱም ይታወሳል፤ ምንም እንኳን መንግስት ሪፖርቱን ቢያስተባብልም፡፡
ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ብዙሃን መናኛዎች መግለጫን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ “በክልሉ ርሃብ አለ ለማለት የሚያስችሉ ሁኔታዎች የሉም” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡