በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ህዝብ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ ሪፖርት አድርጎ ነበር
በርካታ የትግራይ አካባቢዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ተናገሩ፡፡ዋና ጸሃፊው የትግራይ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ለመግታት ሰብአዊ እርዳታ ማዳረስ እንዲሁም በቂ ፈንድ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ዋና ጸሃፊው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት አስታውቋል፡፡
"አሁን የሚከናወኑ ተግባራት ለበርካታ ሰዎች የመኖርና አለመኖር ጉዳይ መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው"ም ነው ያሉት የተ.መ.ድ ዋና ጸሃፊው አንቶንዮ ጉተሬዝ፡፡
የጉተሬዝ ትግራይን የተመለከተ መግለጫ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ያሉ የግጭቱ ተዋናዮች ተኩስ እንዲያቆሙና ያልተገደበ የስብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር ጥሪ እያደረገ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ/ኦቻ/ እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑንና በኢትዮጵያ ከ1970ዎቹ ወዲህ ከፍተኛ የረሀብ አደጋ እንዳንዣበበ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መሪዎችና ተቋማት ለብሔራዊ እርቅና መግባባት ቅድሚያ ሰጥተው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በማቆም ለውይይት እና ለጋራ ሀገራዊ ጉዳይ እንዲሰሩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በቅርቡ ጥሪ ማቅረባቸውም እንዲሁ፡፡
የተለያዩ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ለትግራይ ክልል ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ከነዚህ በቅርቡ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች በክልሉ ያለውን ችግር ለማቃለል በሚል የ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ተፈጠረውን ቀውስ ለመግታት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ በተለያዩ ጊዝያት ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ህዝብ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ ሪፖርት አድርጎ ነበር፡፡