በመጀመሪያው የረመዳን ቀን 70ሺ አማኞች በአል-አቅሳ መስጅድ መገኘታቸው ተገለጸ
የእስራኤል ኃይሎች በሽዎች የሚቆጠሩ አማኞች ከዌስትባንክ ወደ እየሩሳሌም እንዳይገቡ ክልከላ ማድረጋቸው ተገልጿል

የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች በእየሩሳሌም በሚገኘው መስጅድ ዙሪያ ያሉ ቁጥጥሮችን አጠናክረዋል ተብሏል
በኢየሩሳሌም የሚገኘው የእስላማዊ ኢንዶውመንት ዲፓርትመንት እንደገለጸው በመጀመሪያው የረመዳን ቀን 70ሺ አማኞች በአል-አቅሳ መስጅድ ተገኝተው የኢሻና ትራዊህ ጸሎት አድርገዋል።
አል-አስቃ መስጅድ መድረስ የቻሉት አብዛኞቹ የቅድስቷ ከተማ ነዋሪዎችና በ1948 በተካለለው ግዛት ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ናቸው ተብሏል። የእስራኤል ኃይሎች በሽዎች የሚቆጠሩ አማኞች ከዌስትባንክ ወደ እየሩሳሌም እንዳይገቡ ክልከላ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በአካባቢው ያሉ ምንጮች እንደገለጹት የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች በመስጅዱ ዙሪያ በተለይም በባብ አል-አሞንድና ባብ አል-አስባት ያሉ ቁጥጥሮችን አጠናክረው የአማኞችን ማንነት በመፈተሽና በርካታ ወጣቶች እንዳይገቡ በመከልከል የአማኞችን ቁጥር ቀንሰዋል።
በማዕከላዊ ዌስባንክ የሚገኘውና ከ16 የፍልስጤም ግዛት አንዱ የሆነው የእየሩሳሌም ግዛት አስተዳደር እስራኤል ከዌስትባንክ ለጁምኣ ጸሎት ወደ አል-አቅሳ የሚገቡትን አማኞች ቁጥር 10ሺ ብቻ ልታደርግ፣ በቅርቡ ከእስር የተለቀቁትን ላታስገባና በሚገቡት ላይም የእድሜ ገደብ ልታስቀምጥ እንደምትችል አስጠንቅቋል።
አስተዳደሩ አማኞች በሚገቡባቸውና በሚወጡባቸው ቦታዎች በሚገኙ 82 መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ 3ሺ የእስራኤል ወታደሮች ተሰማርተዋል ብሏል።
አስተዳደሩ አለምአቀፍ ስምምነቶች ለማምለክ ነጻነት ዋስትና እንደሚሰጡና የእስራኤል ኃይሎች ኃይማኖታዊ ስነስርአት ወደሚካሄድበት ቦታ እንዳይገቡ እንደሚከለክል አስታውሰዋል። እስራኤል ይህን የምታደርገው የአል-አስቃን መስጅድ ጥንታዊነት ለመቀየርና የተስፋፊነት እቅዶቿን ለማስፈጸም ነው ሲል ከሷል።