“የምነጋገረው የደም መፋሰስን ማስቆም ከሚፈልግ መሪ ጋር ብቻ ነው”- ትራምፕ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በኋላ ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጋር ሊወያዩ የሚችሉበትን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል

በፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እና ዶናልድ ትራምፕ መካከል የተደረገውን ከፍተኛ ፍጥጫ ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ውጥረት ከፍ ብሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እና የዩክሬኑ አቻቸው ቮለድሚር ዘለንስኪ ሀይለ ቃል የተቀላቀለበት በኋይት ሀውስ በመገናኛ ብዙሀን ፊት የተደረገው ውይይት መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
በጦርነት ማቆም እና በዩክሬን ውድ ማዕድናት አጠቃቀም ዙሪያ ለመወያየት ወደ ዋሽንግተን ያቀኑት ዘለንስኪ ከትራምፕ አስተዳደር የገጠማቸውን ያልተጠበቀ ፍጥጫ ተከትሎ ጉብኝታቸውን ቀደም ብለው አጠናቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በጦርነቱ አካሄድ ፣ አሜሪካ በፑቲን ላይ የተለሳለሰ አቋም ማሳየቷ ተገቢ እንዳልሆነ ያደረጉት ንግግር ከትራምፕ እና ከምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞታል፡፡
ትራምፕ ዘለንስኪን “አሜሪካን አላከበርክም ያለእኛ ድጋፍ ጦርነቱ አይደለም ሶስት አመት ሶስት ሳምንት አይቆይም ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በመሪዎቹ ውይይት ዙሪያ የነቀፋ እና የድጋፍ ድምጾች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰሙ ነው፡፡
ከሁለቱ መሪዎች ዱላ ቀረሽ ንግግር በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያረጉት ትራምፕ “ከዚህ በኋላ የምንገጋገረው ደም መፋሰስን ማስቆም ከሚፈልግ መሪ ጋር ብቻ ይሆናል” ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከዘለንስኪ ጋር የሚያደርጉት ቀጣይ ውይይት “ሰላም የማስፈን ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን አንደሚገባው” ቅድመ ሁኔታን አስቀምጠዋል፡፡
በተጨማሪም “የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከሩስያ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እውነተኛ ፍላጎት አላሳዩም” ሲሉ ከሰዋቸዋል፡፡
“የምንፈልገው ሰላም ነው ሀይሉን ለመሳየት እና ድፍረት ስላለው ብቻ ሰላምን ባለመፈለግ ብቻ ውጊያን መቀጠል ከሚመኝ ሰው ጋር መነጋገር አንፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“በውግያ ውስጥ ለ10 አመታት መዝለቅ አንፈልግም” ያሉት ትራምፕ “የአሜሪካ ድጋፍ ዘለንስኪ የድርድር ሀሳቦችን እንዳይቀበል ጠንከራ የሚያደርገው ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ የተኩስ አቁም ጉዳይ አፋጣኝ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን እንዳለበት ገልጸው ዘለንስኪ “ይህንን ለማገናዘብ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን” ጠቁመዋል።
አክለውም ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በተሻለ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሰላም ለመፍጠር ፍቃደኛ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን የአሜሪካ ፖሊሲ ጦርነቱን ከማራዘም ይልቅ መረጋጋት ላይ ማተኮር እንዳለበት አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው ከውይይቱ በኋላ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይቅርታ የሚጠይቁበት ምክንያት እንደሌለ እንዲሁም ለአሜሪካ መንግስት እና ህዝብ ከፍተኛ ክብር እንዳላቸው ግልጸዋል፡፡