ግብጽ የቀይ ባህር አካል ያልሆነ ማንኛውም ሀገር በባህሩ ላይ የባህር ሀይል እንዲያቋቁም አልፈቅድም አለች
ካይሮ ይህን ያለችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ በኤርትራ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ ነው

ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር የራሷን ወደብ ለማግኘት እና የባህር ሀይል ለመቋቋም እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል
ግብጽ የቀይ ባህር አካል ያልሆነ ማንኛውም ሀገር በባህሩ ዙሪያ የሚያደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና የባህር ሀይል ለማቋቋም የሚደረግ ጥረት እንደማትቀበል አስታወቀች፡፡
ይህ የተባለው በግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዳላቲ የተመራ ልዑክ በኤርትራ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ውይይት ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡
በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት የቀይ ባህርን ጨምሮ የጋራ በሚያደርጓቸው ቀጠናዊ እና በተለያዩ መስኮች የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ተስማተዋል፡፡
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር “የቀይ ባህር ደህንነት በተዋሳኝ ሀገራቱ ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው ፤ምንም አይነት ወታደራዊም ሆነ የባህር ሃይል በአካባቢው መገኘትን አንፈቅድም” ብለዋል።
አክለውም “ወደብ አልባ ሀገራት በቀይ ባህር ዙሪያ የባህር ሀይል ማቋቋም የቀጠናውን እና የባህሩን ደህንነት ለመጠበቅ የተደረሰውን ስምምነት ክፉኛ የሚጎዳ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ እንዳስታወቀው አብዳላቲ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በአህጉራዊ የጋራ ጉዳዮች በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ደህንነትን መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፣ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሉዓላዊነቷን በሁሉም ግዛቶቿ ላይ ለማስረፅ የሚያስችል የሃሳብ ልውውጥ ተካሂዷል።
ስብሰባው በሊቢያ እና በአፍሪካ ሳህል አካባቢ ስላለው ሁኔታ እንዲሁም በቀይ ባህር ውስጥ ያሉ ለውጦች እና ማንኛውም ቀይ ባህር አካል ያልሆነ መንግስት በፀጥታ እና በአስተዳደር ውስጥ ተሳትፎን ውድቅ በማድረግ ላይ ትኩረቱን አድርጓል ።
በተጨማሪም በጥቅምት 2024 በኤርትራ ከተካሄደው የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤ በኋላ ተመሳሳይ የሚኒስትሮች ስብሰባዎችን በሞቃዲሾ እና በአስመራ ለማካሄድ እና በቅርቡ ለሁለተኛው የፕሬዝዳንት ጉባኤ ለመዘጋጀት መምከራቸውን አብዳላቲ ጠቁመዋል።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በበኩሉ ትላንት ምሽት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዳላቲ ከተመራ ልዑካን ጋር በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይቶች ማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡
በሱዳን ሶማሊያ እና በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በቀይ ባህር አካባቢዎች የሰላም እና የደህንነት ፈተናዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት መካሄዱንም መግለጫው አክሏል፡፡
ግብፅና ኤርትራ በሶማሊያ ጉዳይ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃገብነት ውድቅ በማድረግ የሞቃዲሾን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንደሚደግፉ በተደጋጋሚ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ለባህር ሀይል እና ለንግድ የሚሆን 20 ኪሎሜትር የሚሸፍን የባህር ዳርቻ ለመከራየት የመግባብያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል፡፡
በጥር ወር በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መሪዎች የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ ተስማማተዋል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ የጎረቤታሞቹ ሀገራት ከፍተኛ መሪዎች በሞቃዲሸ እና በአዲስ አበባ የተገናኙ ሲሆን ከሰሞኑም የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሞቃዲሾ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡