በቡግና ወረዳ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ከህጻናትና እናቶች አልፎ በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እየታየ መሆኑን ነዋሪዎች ተናሩ
ከዚህ ቀደም በወረዳው 10 ሺ እናቶች እና ህጻናት ከምግብ እጥረቱ ጋር በተያያዘ መጎዳታቸው መዘገቡ ይታወሳል

አል ዐይን አማረኛ ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪውች የምግብ እጥረቱን ተከትሎ በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ህጻናት እና እናቶችን ጨምሮ 10 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ከአራት ወራት በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በክልሉ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት መካከል በተፈጠረው ግጭት ከአንድ አመት በላይ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው የቡግና ወረዳ ከግጭቱ በተጨማሪ አካባቢው ያጋጠመው የተፈጠሮ አደጋ ለችግሩ መንስኤ መሆኑን አል ዐይን አማርኛ ከወረዳው አስተዳደር ያገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
አካባቢው ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚከሰትበት ቦታ በመሆኑ በ2016/17 የምርት ወቅት ያጋጠመው ጎርፍ እና የምርት በበረዶ መመታት ሁኔታውን አባብሶት ቆይቷል፡፡
በወቅቱ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መድሀኒቶችን፣ አልሚ ምግቦች እና ሌሎች መሰረታዊ ቁሳቁሶችን ማድረስ ባለመቻሉ 65 በመቶ የወረዳው ህፃናት እና 84 በመቶ እናቶች በአጣዳፊ የምግብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኙ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም በወረዳው ከወራት በኋላ የእርዳታ ስርጭቱ እና የምግብ አቅርቦቱ ምን ይመስላል በሚል አል ዐይን አማርኛ ባደረገው ማጣራት የአቅርቦት እጥረት መኖሩን ከነዋሪዎቹ ማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ሀረገወይን ዘመነ የወረዳው ነዋሪ ናቸው እሳቸው እንደሚሉት ጉዳዩ በሚዲያ ከተዘገበ በኋላ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ለእናቶች እና ህጻናት ቅድሚያ በመስጠት ድጋፍ መሰራጨት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እርዳታው ተከታታይ ባለመሆኑ አሁንም በርካቶች በጉዳት ላይ ናቸው፡፡
“በየቀበሌው አንጀታቸው የተጣበቁ ህጻናት ቁጥር ትንሽ አይደለም በመጀመሪያ ሰሞን አልሚ ምግቦችን መጥተው ለመደገፍ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም ከጉዳት መጠኑ አንጻር በአንድ እና ሁለት ጊዜ ድጋፍ የሚሻሻል አይደለም፤ ህጻናቱ ሰውነታቸው በመጎዳቱ ተከታታይ ህክምና እና የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል፡፡
ወይዘሮ እታለም ወዳጆ የተባሉ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ቀደም ሲል የምግብ እጥረቱ በስፋት ይታይ የነበረው በህጻናት እና እናቶች ላይ ቢሆንም አሁን ግን በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችም በችግር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
“በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የጉልበት ስራ ሌላም ነገር ሰርተው ራሳቸውን ለመደጎም ጥረት ያርጉ ነበር አሁን ግን ሁሉም በሚባል ደረጃ ለምግብ እጥረቱ በመጋለጡ ሁሉም የሰው እጅ ጠባቂ ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ድጋፉ አንዳንድ ጊዜ በወር አንድ ጊዜ ሌላ ጊዜ ደግሞ በወር ሁለት ጊዜ ብቻ እንደሚመጣ እና ማህበረሰቡ ከሚገኝበት ችግር አንጻር አሁንም በቂ አለመሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ሁለት እና ሶስት የቤትሰብ አባል ለሚገኝበት ቤት የሚሰጠው ድጋፍ ከሳምንት የማያሻግር መሆኑን የሚያነሱት ወይዘሮ እታለም የሚሰጠው 15 ኪሎ ነጭ ዱቄት በቂ ባለመሆኑ ከሳምንታት በኋላ ተመሳሳይ ችግር ላይ እንደሚወድቁ ገልጸዋል
በወረዳው ብርኮ የተባለው ቀበሌ ነዋሪ አቶ ግርማ ቅባቴ እንደሚሉት “በጤና ጣብያዎች እና በየቤቱ ርሀብ ጎድቷቸው የሚገኙ ሰዎችን መመልከት ያሳቅቃል ችግሩ እንደተከሰተ አካባቢ በጥናት የተለዩ እና በጤና ጣብያዎች ገብተው ህክምና ማግኘት የሚገባቸው እናቶች እና ህጻናት በቦታ ጥበት ምክንያት ሁሉም አልገቡም”፡፡
አቶ ግርማ አክለውም “ችግሩ አሁን ከሚገኝበት ስፋት አንጻር በመጪው ክረምት እርሻ ታርሶ ማህበረሰቡ ትንሽ ማገገም የሚችልበትን አቅም እስከሚያገኝበት እስከመጪው ህዳር እና ታህሳስ ድረስ ቋሚ ድጋፍ የማይደረግ ከሆነ የከፋ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል” ነው የተናገሩት፡፡
በሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ ለተከሰተው ርሀብ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች አሉ፡፡
ከነዚህ መካከል የማዳበሪያ በወቅቱ አለመደረስ፣ ከመጠን ባለፈ ዝናብ እና በረዶ ምርት መመታት እንዲሁም በመንግስት እና ፋኖ ሀይሎች መካል እየተደተረገ በሚገኘው ውግያ ምክንያት በቂ ምግብ አለመድረስ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የምግብ እጥረቱ በመገናኛ ብዙሀን ከተዘገበ በኋላ ለወረዳው የሚላኩ የእርዳታ ግብአቶችን በሃላፊነት ተቀብሎ ለማከፋፈል ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከወረዳው የትምህርት ፣ የጤና እና የግብርና ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ የድጋፍ ስርጭት ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡
የዚህ ኮሚቴ አባል የሆኑት መላከ ብርሀን ዮሴፍ ኮሚቴው በሰባቱም ቀበሌ ተዘዋውሮ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 110 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች የምግብ እጥረት እንዳለባቸው እና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
“በተጠናው ጥናት መሰረት 68 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፤ በአሁኑ ወቅት በአንድ ጤና ጣቢያ ቁጥራቸው እስከ 30 የሚደርሱ ህጻናት እና እናቶች ተኝተው ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል ቀሪዎቹ ደግሞ ቤታቸው ሆነው ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየተሞከረ ነው” ብለዋል፡፡
መላከ ብርሀን ዩሴፍ እንደሚሉት ሁሉም በምግብ እጥረት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ህጻናት እና እናቶች በጤና ተቋም ተኝተው ክትትል ሊደረግላቸው ቢገባም ባለው የአቅርቦት እና የቦታ ጥበት የተነሳ ወረፋ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የአማራ ልማት ድርጅት (አመልድ) ሰፊውን የምግብ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም አሁን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ድጋፉን አቁሟል፡፡
ቀይ መስቀል፣ ዩኒሴፍ፣ እና የአለም ምግብ ፕሮግራም ለአንድ ጊዜ የሚሆን የአስቸኳይ እርዳታ ካደረጉ በኋላ ለወረዳው ድጋፍ አለመላካቸውም ተነስቷል፡፡
“ወደ 20 የሚደርሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወደ ወረዳው ገብተው የጉዳት ግምገማ አድርገው የነበረ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ የሚጨበጥ ድጋፍ ያደረጉት አምስት አይሞሉም፡፡ አሁን ላይ የእርሻ ጊዜ አልፏል የአየር ሁኔታው ከተስተካከለ እንዲሁም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ለእርሶ አደሩ የሚደርሰው ከሆነ ዘርቶ ራሱን በምግብ ሊደግፍ የሚችለው በመጪው አመት ነው ስለሆነም ለአንድ አመት የሚሆን እርዳታ ያስፈልገዋል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከመስከረም 19 ጀምሮ የባንክ አገልግሎት መቋረጥ ፣ የሰው እና የእንስሳት መድሀኒት እጥረት እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውሀ እጥረት በወረዳው ተጨማሪ ችግር መሆኑ ተነግሯል፡፡
በመሆኑም ተጨማሪ ሞት እና የከፋ ጉዳት ከማጋጠሙ በፊት መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የእርዳታ ድርጅቶች ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ የወረዳው ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በነዋሪዎች የተነሳውን የእርዳታ አቅርቦት እጥረት በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ከወረዳው እና ከክልሉ የመንግስት አመራሮች መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።