በጦርነት ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው የነበሩ 728 ህጻናትን ማገናኘቱን ተመድ ገለፀ
በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የሚገኙ 786 ሺህ ሰዎች እርዳታ እንዲያገኙ ማደረጉንም ተመድ አስታውቋል
በሶስቱ ክልሎች ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ከ1 ሺህ ለሚበልጡና ሴቶች የጤና አገልግሎት እያገኙ ነውም ብሏል
በጦርነት ምክንያት በትግራይ እና አማራ ክልሎች “ከወላጆቻቸው የተለዩ 728 ህጻናትን እንዲገኛኙ ማድረጉን የተባሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ /ኦቻ/ ባወጣው ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በርካታ ህጻናት ከወላጆቻቸው መለያየታቸውን አመላክቷል።
ከወላጆቻቸው የተለያዩ ህጻናት መጠን፤ ከደረሰው አጠቃላይ ጉዳት 9 በመቶውን ይሸፍናልም ነው ያለው ኦቻ በሪፖርቱ።
ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ህዳር መጨረሻ ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ በሶስቱ ክልሎች ከ1 ሺህ የሚበልጡ ጾታን መሰረት ካደረገ ጥቃት ደርሶባቸው በህይወት የተረፉ ሰዎች በጤና አገልግሎት ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ኦቻ አስታውቋል።
500 ሺህ ገደማ ለሚሆኑ ህጻናት ሰፊ የአመጋገብ ዘመቻ ለማካሄድ ከ5 ሺህ 700 በላይ የቫይታሚን ኤ እሽጎች ወደ አፋር ክልል መላኩንም ኦቻ በሪፖርቱ ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ/ኦቻ/ አክሎም፤ “በአማራ ክልል ከ560 ሺህ በላይ፣ በአፋር ከ88 ሺህ በላይ እንዲሁም በትግራይ ክልል ከ138 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ ተደርጓል” ለሏል።
ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት 24 አንድ አመት አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ቢችልም ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ጦሩን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል።
መንግስት ይህን ቢልም፤ ህወሓት የመንግስት ጦር እንዲወጣ ማድረጉን በወቅቱ ገልጾ ነበር። ህወሓት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት በርካታ ቦታዎች መቆጣጠርም ችሎ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ በህወሃት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታዎች ነጻ ወጥተዋል።
መንግስት የህወሓት ሀይሎችን በማሸነፍ ይዘዋቸው ከነሩ ቦታዎች እንዲወጡ ማድረጉን ሲገልጽ ህወሓት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ይገልጻል።
ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነቱ በሺዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል።