ተመድ መጋዘኖቹ “በህወሓት ኃይሎች” መዘረፋቸውን ተከትሎ በኮምቦልቻና ደሴ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ አቆመ
ዝርፊያውን ጨምሮ በሰራተኞቼ ላይ የሚደርሰው ማስፈራርያና ዛቻ እርዳታውን እንዳቆም አስገድዶኛልም ነው ደብሊው ኤፍ ፒ ያለው
በአማራ ክልል በሚገኙ መጋዘኖቹ መዘረፍ ምክንያት በሁለቱ ከተሞች ያደርግ የነበረውን እርዳታ ማቆሙን ድርጅቱ አስታውቋል
በእርዳታ ማከማቻ መጋዘኖቹ መዘረፍ ምክንያት በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚያደርገውን የምግብ ድጋፍ ማቆሙን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡
ፕሮግራሙ ከዛቻ እና ማስፈራሪያ አልፎ ጠብመንጃ የተደገነባቸው ሰራተኞቹ ዝርፊያውን ለማስቆም አለመቻላቸውን አስታውቋል፡፡
መንግስት በህወሓት ተይዘው የነበሩትን ደሴና ከምቦልቻ ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ
ትናንት ረቡዕ በነበራቸው መግለጫ ጉዳዩን የተመለከተ ሃሳብ ያነሱት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ኮምቦልቻ ከሚገኙ የፕሮግራሙ መጋዘኖች የህጻናት ምግብን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች መዘረፋቸውን ተናግረዋል፡፡
“በትግራይ ኃይሎች እና በአንዳንድ ነዋሪዎች መፈጸሙ የተነገረለት የምግብ ዘረፋ የኋላ ኋላ ተባብሶ ኮምቦልቻ የሚገኙ መጋዘኖችን እስከመዝረፍ ደርሷል”ም ነው ቃል አቀባዩ ያሉት፡፡
“በታጠቁ ኃይሎች በሰብዓዊ የእርዳታ ሰራተኞች ላይ የሚደረጉ እንዲህ ዓይነት ትንኮሳዎች ተቀባይነት የላቸውም፤ ድርጅታችንን ጨምሮ በሁሉም አጋሮቻችን የሚደረጉ ሰብዓዊ ጥረቶችን ያቀዛቅዛሉ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዱጃሪች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 9.4 ሚሊዮን ሰዎች በሚገኙበት በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ያለውን የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የበለጠ እንደሚያባብሰውም ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ሶስት የፕሮግራሙ ተሽከርካሪዎች ለወታደራዊ ግልጋሎቶች መዋቸውን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ድርጊቱን በማውገዝ ሁሉም የግጭቱ ተዋናዮች የእርዳታ ሰራተኞችን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
ሆኖም ሰብዓዊ እርዳታዎችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ከገቡ የተመድ ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ እንዳልተመለሱ በራሱ በድርጅቱ በመንግስትም ጭምር መገለጹ ይታወሳል፡፡
ተመድ መስከረም ላይ መቀሌ ከደረሱ 149 የርዳታ ተሽከርካሪዎቹ መካከል የተመለሰ እንደሌለ በማስታወስ ከሃምሌ መባቻ ጀምሮ ወደ ትግራይ ከገቡ 466 ተሽከርካሪዎቹ 38ቱ ብቻ መመለሳቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡